ዩኤኢ እና ኢትዮጵያ ባህላዊ እሴቶቻችንን ለማልማትና ለማስተዋወቅ በጋራ እንሰራለን አሉ
የሃገራቱን ባህልና ጥበብ ለዓለምማስተዋወቅ ላይ ያተኮረ የበይነ መረብ ውይይት ተካሂዷል
ሃገራቱ እሴቶቻቸውን ከማልማትና ማስተዋወቅ ባለፈ የ“ፐብሊክ ዲፕሎማሲ” ግንኙነታቸውን ለማጠናከር ተስማምተዋል
የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች (ዩኤኢ) እና ኢትዮጵያ ባህላዊ እሴቶቻችንን ለማልማትና ለማስተዋወቅ በጋራ እንሰራለን አሉ፡፡
ሃገራቱ ያላቸውን ባህልና ጥበብ ለማስተዋወቅ በሚችሉበት ሁኔታ ላይ ያተኮረና በኢትዮጵያ የዩኤኢ ኤምባሲ አማካኝነት “Dialogue on Arts & Culture of the UAE & Ethiopia” በሚል ርእስ የተዘጋጀ የበይነ መረብ ውይይት ተካሂዷል፡፡
በውይይቱ የተለያዩ ጽሁፎች ቀርበዋል፡፡ በጽሁፎቹ ሁለቱም ሀገራት የቱባ ባህል እና ጥበብ ባለቤት መሆናቸው ተነስቷል፡፡
በርካታ ሀገራት ያላቸውን ባህልና ጥበብ ለዓለም በማስተዋወቅ ስትራቴጂያዊ ጥቅማቸው እንደሚያስጠብቁና ገጽታቸውን እንደሚገነቡ በቀረቡት ጽሁፎች የገለጸ ሲሆን ኢትዮጵያና ዩኤኢ ይህንኑ ሊያደርጉ እንደሚገባም ተጠቆሟል፡፡
በኢትዮጵያ ዩኤኢ ኤምባሲ የፖለቲካ፣ኢኮኖሚና የሚድያ ጉዳዮች ኃላፊ ታላል አል አዚዚ ዩኤኢ ያላትን ባህልና ጥበብ ለዓለም በማስተዋወቋ ዓለም ለዩኤኢ ባህል እና እሴቶች ያለው ምልከታ ይበልጥ እንዲጎለብት ከፍተኛ ሚና ነበረው ብለዋል፡፡
“ዩኤኢ በሰራችው ስራ አሁን የአረቡ ዓለም የጥብብ ማእከል ለመሆን ችላለች”ም ነው ያሉት፡፡
በመሆኑም ሃገራቸው ይህን ልምዷን ለማካፋልና ከኢትዮጵያ ጋር ለመስራት፤ ያላትን የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ግንኙነት ለማጠናከር ፍላጎት እንዳላትም ጭምር ገልጸዋል፡፡
የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴርን ወክለው በበይነ መረብ ውይይቱ የተሳተፉት አቶ ተፈሪ ተክሉ በበኩላቸው ኢትዮጵያ የቱባ ባህል፣ጥበብ እና ቋንቋዎች ሀገር መሆኗ አንስተዋል፡፡
ይህን ለዓለም በማስተዋወቅ ከሀገራት ጋር ያላትን የፐብሊክ ዲፐሎማሲ ግንኙነት ለማጠናከር ትልቅ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች መሆኗንም ገልጸዋል፡፡
ከዩኤኢ ጋር ይህንኑ የማጠናከር ፍላጎት እንዳላትና እንደምትሰራም ነው አቶ ተፈሪ የተናገሩት፡፡
“ፌስቲቫሎች፣ የባህል ቀናት፣ የጥበብ ጉብኝቶች፣ የልምድ ልውውጦች፣ ስልጠናዎች እና ኤግዚብሽኖች ሁለቱም ሀገራት ያለቸውን የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ግንኙነት ለማጠናከርና ያላቸውን ባህል ለማስተዋወቅ ሊተባበሩባቸው የሚችሉ መስኮች ናቸው”ም ብለዋል፡፡
በውይይቱ አዲስ ፋይን አርትን ጨምሮ የተለያዩ ሚድያዎች የወከሉ አካላት ተሳታፊዎች ሆነዋል፡፡