ዩኤኢ በአዲስ አበባ ለ 3 ሺህ አባወራዎች የምግብ ድጋፍ አደረገች
ባሳለፍነው ሳምንት ከሶማሌ ክልል ተፈናቅለው ገላን ለሚገኙ ዜጎች መሰል ድጋፍ መደረጉ የሚታወስ ነው
ድጋፉ ዩኤኢ ለቀጠናው የምታደርገው የእርዳታ ፕሮጄክት አንዱ አካል ነው
የተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች (ዩኤኢ) ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ከ11 የአዲስ አበባ ክ/ከተማዎች ለተውጣጡ የህብረተሰብ ክፍሎች ድጋፍ አደረገች፡፡
በዛሬው ዕለት በአበበ ቢቂላ ስታዲየም በተደረገው ዝግጅት ለተረጂዎች የደረቅ ምግብ እርዳታ የተሰጠው ፣ በዩኤኢ ሞሃመድ ቢን ራሺድ አል-ማኽቱም ግሎባል ኢንሼቲቭ እና በኢትዮጵያ የዩኤኢ ኤምባሲ አማካኝነት ነው፡፡
በዚህም በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ላሉ ሦስት ሺህ የህብረተሰብ ክፍሎች የዘይት፣ ሩዝ፣ ዱቄትና ቴምር እርዳታ ተሰጥቷል፡፡
በመርሀ ግብሩ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ የእሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር ሰሎሞን ፍስሀ ፣ የዛሬውን ጨምሮ ዩኤኢ እያደረገች ላለው ሁለንተናዊ ድጋፍ አመስግነዋል፡፡
“እየተደረገ ያለው ድጋፍ ዩኤኢ ለቀጣናው የምትሰጠው እርዳታ አንድ አካል ነው ፤ እናም በኢትዮጵያ የምናደርገው ድጋፍ ቀጣይነት ይኖረዋል ”ያሉት ደግሞ በኢትዮጵያ የዩኤኢ ኤምባሲ የባህል ጉዳዮችና ዲፕሎማሲ ክፍል ኃላፊ ዓሊ አልጋፍሊ ናቸው፡፡
የአዲስ አበበ ከተማ ከንቲባ ጽ/ቤት የውጭ ግንኙነት ኃላፊ አብርሃም አስራት በበኩላቸው የእርዳታ መርሀ-ግብሩን ላዘጋጀው ኤምባሲ የከተማ መስተዳደሩ ከፍተኛ ምስጋና አለው ብለዋል፡፡ በቀጣይም መስተዳደሩ ከኤምባሲው ጋር በትብብር ለመስራት ዝግጁ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች (ዩኤኢ) ፣ በሞሃመድ ቢን ራሺድ አልማኽቱም ግሎባል ኢንሼቲቭ በኩል ከሶማሌ ክልል ተፈናቅለው ገላን ለሚገኙ ኢትዮጵያውያን ዜጎች ባሳለፍነው ሳምንት ድጋፍ ማድረጓ ይታወሳል፡፡
ዛሬ የተደረገው ድጋፍም የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ለአንድ መቶ ሚሊዬን የዓለማችን ዜጎች የደረቅ ምግብ እርዳታ ለማድረግ የያዘቸው “መቶ ሚሊዮን ምግቦች/100 Million meals” ፕሮጀክት አካል መሆኑ ነው የተገለጸው፡፡