ዩኤኢ በአየር ንብረት ለውጥ መስክ ከኢትዮጵያ ጋር ለመስራት ፍላጎት እንዳላት ገለጸች
መንግስት ኢትዮጵያ 104.99 ሚልዮን ሜትሪክ ቶን ካርቦን ዳይ ኦክሳይድ መቀነስ መቻሏን ገልጸዋል
የአፍሪካ ቀንድ የአከባቢ ማእከል ዘላቂ የሆነ የኢኮኖሚ ልማት ለማረጋገጥ ምርምሮች እያካሄድኩ ነው ብለዋል
የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ (ዩኤኢ) በአየር ንብረት ለውጥ መስክ ከኢትዮጵያ ጋር ለመስራት ፍላጎት እንዳላት በኢትዮጵያ የዩኤኢ ኤምባሲ የአፍሪካ ጉዳዮች ተወካይ ታላል አል-አዚዚ ገለጹ፡፡ ታላል አል-አዚዚ ይህንን ያሉት የአየር ንብረት ለውጥን በማስመልከት በተዘጋጀውና የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በተሳተፉበት የበይነ መረብ ውይይት ላይ ነው፡፡
በውይይቱ የአየር ንብረት በተመለከተ በኢትዮጵያ እየተከናወኑ ስላሉ ተግባራት፣ የተገኙ ውጤቶች እና ተግዳሮቶችን የሚያዳስሱ ጽሁፎች ቀርበዋል፡፡
የአካባቢ፣የደንና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን በመወከል መነሻ ጽሁፍ ያቀረቡት አቶ መንሱር ደሴ ኢትዮጵያ እንደ ጎርፍ እና ድርቅ የመሳሰሉ አደጋዎች በተደጋጋሚ ቢያጋጥሟትም የአየር ንብረት ለውጥ ዙርያ የአረንጓዴ ኢኮኖሚን በመንደፍ በርካታ ስራ እያከናወነች መሆኗን ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ እስካሁን ባከናወነቻቸው ተግባራት 104.99 ሚልዮን ሜትሪክ ቶን ካርቦን ዳይ ኦክሳይድ መቀነሷ፣ የአስር አመት የልማት መርሀ-ግብር ማቀዷ እንዲሁም ከ20 ሚልዮን በላይ ለሚሆኑ ዜጎቿ አየር ንብረትን በተመለከተ ግንዛቤ እንዲኖራቸው መስራቷ በስኬት ሊነሳ የሚችል ነውም ነው ያሉት አቶ መንሱር፡፡
ኢትዮጵያ የአየር ንብረት የተመለከቱ እንደ ኪዮቶ ፕሮቶኮል እና ፓሪስ ስምምነቶች ፈርማ ማጽደቋን ያስታወሱት አቶ መንሱር አሁንም ቢሆን የዓለም የአየር ንብረት ፎሮሞች ከመምራት እንዲሁም በሁለትዮሽና ባለብዙ መድረኮች በመሳተፍ የምታበረክተው አስተዋጽኦ አጠናክራ ትቀጥልበታለች ብሏል፡፡
ሌላው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን በመወከል ጽሁፍ ያቀረቡት የአፍሪካ ቀንድ ኢንቫይሮሜንት ማእከል /Horn of Africa Regional Environment Centre/ ዳይሬክተር ሞክርያ አርጋው በበኩላቸው የሚመሩት ተቋም ዘላቂ የሆነ የኢኮኖሚ ልማት ለማረጋገጥ እና የታዳሽ ኃይል ተደራሽነትን ለማስፋት የሚያስችሉ ጥናቶች እያከናወነ መሆኑን ተናግሯል፡፡
አቶ ሞክርያ የሚመሩት ማእከሉ በቀጠናው ትርጉም ያለው ለውጥ ለማምጣት እንደ ኬንያ፣ኢጋንዳ እና ሩዋንዳ ከመሳሰሉ ሀገራት እንዲሁም 42 ከሚሆኑ ዩኒቨርሲቲዎች እና ተቋማት ጋር በጥምረት እየሰራ ነውም ብሏል፡፡
በአደስ አበባ ጉለሌ ክ/ከተማ የሚገኘው “ጉለሌ ቦታኒክ ጋርደን” ማእከሉ ከሰራቸው ስረዋች እንደማሳያ የሚጠቀስ ነው ያሉት አቶ ሞክርያ ፐሮጀክቱ እንደ ጥሩ ልምድ ተወስዶ ወደ ሶማሊላነድ መስፋፋቱንም አስታውቋል፡፡
አቶ ሞክርያ ማእከሉ በዘርፉ የሚደረጉ ምርምሮች ለማበረታታት ጥናት አጥኚዎችን እየደገፈ መሆኑንም ተናግሯል፡፡ዩኤኢ ፕሮጀክቶቹን እንድትደግፍም ነው የጠየቁት አቶ ሞክርያ፡፡