አረብ ኤምሬትስ ለአፍሪካ የ4.5 ቢሊዮን ዶላር ታዳሽ ኃይል ልማት አጋርነት ይፋ አደረገች
አረብ ኤምሬትስ በአፍሪካ በሚቀጥሉት ዓመታት15 ጊጋዋት ታዳሽ ኃይል ለማልማት መታቀዱን አስታወቀች
የኮፕ28 ፕሬዝዳንት አፍሪካ ለአየር ንብረት መከላከልና መቋቋም በየዓመቱ የሚያስፈልጋትን 250 ቢሊዮን ዶላርን ለማሰባሰብ እንደሚሰሩ ተናገሩ
አረብ ኤምሬትስ የአፍሪካን የታዳሽ እምቅ ኃይል የሚያለማ አጋርነት አስተዋውቃለች። ሀገሪቱ ከአፍሪካ ጋር ዘላቂ ኃይል ለማልማት የሚያስችል አዲስ ስልታዊ አጋርነት ይፋ አድርጋለች።
አረብ ኤምሬትስ አዲስ “ዘላቂ ብልጽግና” ያለችውን የአጋርነት እርምጃ ያሳወቀችው ናይሮቢ እየተካሄደ በሚገኘው የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ ላይ ነው።
የዓለም የአየር ንብረት ጉባኤ ኮፕ28 ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሱልጣን አል ጃበር በጉባኤው ላይ ባደረጉት ንግግር “አዲስ የሽግግር አጋርነት” ለመመስረት ወጥነናል ብለዋል።
በስልታዊ አጋርነቱ በ2030፤ 15 ጊጋዋት ንጹህ ኃይል ለማልማት መታቀዱን አል ጃበር አስታውቀዋል። ለዚህም ሀገራቸው 4.5 ቢሊዮን ዶላር እንደምትመድብ ያሳወቁት የኮፕ28 ፕሬዝዳንት፤ ከተለያዩ አካላት ተጨማሪ 12.5 ቢሊዮን ዶላር ለማሰባሰብም እቅድ እንዳለ ገልጸዋል።
እርምጃው አፍሪካ አስቀድማ ንጹህ ኃይልን በማልማት ለወደፊት እጣ ፈንታዋ መንገድ መጥረግ ያስችላታል ብለዋል።
“ይህ ጅምር ግልጽ የሆነ የሽግግር እቅዶች፣ ጠንካራ የቁጥጥር ማዕቀፎች እና አስፈላጊ የሽግግር መሰረተ ልማት ለመዘርጋት ቁርጠኝነት ያላቸውን ሀገሮች የሚመለከት ይሆናል” ሲሉ ይፋ የተደረገው አጋርነት ያነጣጠረበትን አቅጣጫ አብራርተዋል።
አጋርነቱ “ለአፍሪካ በአፍሪካዊያን” እንዲሆን ታስቦ ይነደፋል ሲሉ ያከሉት አል ጃበር፤ ሀገራቸው በ2030 ታዳሽ ኃይልን በሦስት እጥፍ ለማሳደግ የያዘችውን ዓለም አቀፍ ግብ ያሳድጋልም ብለዋል።
የኮፕ28 ፕሬዝዳንት ዓለም በፓሪስ ስምምነት የግሪን ሀውስ ጋዝን ዜሮ ለማድረስ የተያዘውን አቋም ለማሳካር በሩጫው ወደ ኋላ እየቀረች መሆኑንም ተናግረዋል።
“በተለመደ አሰራር” ጠብ የሚል ነገር የለም ሲሉ ያሰመሩት ፕሬዝዳንቱ፤ ሀገራትን ጥሎ የማይጓዝ፣ እውነተኛና የተቀናጀ እርምጃ እንዲወሰድ ጠይቀዋል።
ከዓለም ሦስት በመቶ ብቻ የልቀት አበርክቶ ያላት ነገር ግን በክፉኛ ድርቅ፣ ጎርፍና በሌሎችን የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖዎች እየተጎዳች ላለችው አፍሪካ መከላከልና መቋቋም የሚያስችል ገንዘብ ለማሰባሰብ ያላቸውን ቁርጠኝነትም ገልጸዋል።
ለዚህም የአፍሪካ ልማት ባንክን አሀዝ ጠቅሰው፤ አህጉሪቱ ለአየር ንብረት መከላከልና መቋቋም በየዓመቱ 250 ቢሊዮን ዶላርን ትሻለች ብለዋል። ሆኖም ግን ከዚሁ ገንዘብ 12 በመቶን ብቻ እንዳገኘች ተናግረዋል።
ሱልጣን አል ጃበር ሀገራትና ለጋሾች ቃል ገቡትን ገንዘብ እንዲያቀርቡ የጠየቁ ሲሆን፤ ይህን ገንዘብም በእጥፍ እንዲያሳድጉ እወተውታለሁ ብለዋል።