ዩኤኢ የቱርክን ወታደር ወደ ሊቢያ የመላክ እቅድ አወገዘች
ዩናይትድ አረብ ኤሚሬትስ (ዩኤኢ) የቱርክ ፓርላማ በትናንትናው እለት ቱርክ ወታደር ወደ ሊቢያ እንድትልክ ማጽደቁን ማውገዟን የኤሚሬትስ ዜና አገልግሎት ዘግቧል፡፡
ድርጊቱ አለምአቀፍ ህግን በግልጽ የሚጥስ መሆኑንም ዩኤኢ አስታውቃለች፡፡
የዩኤኢ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ የተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት እ.ኤ.አ በ2011 በሊቢያ ጉዳይ ያወጣውን ህግ ይጥሳል ብሏል፡፡
የቱርክ ዉሳኔ በወንድማማች አረብ ሀገራት መካከል ያለውን ግንኙነት የሚያሻክር መሆኑን ያስታወቀው መግለጫው የቱርክ ወታደራዊ ጣልቃገብነት የሚያስከትለው መዘዝ እንደሚኖርም አስጠንቅቋል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንደዚህ አይነት ወታደራዊ ጣልቃገብነት የአረብ ሀገራትን ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥል እንዲሁም በሜዲትራኒያን አካባቢ ያለውን ሰላም ሚያናጋ መሆኑንም ገልጿል፡፡
ቱርክ ጣልቃገብነቷን ምክንታዊ ለማድረግ የምትሄድበትን መንገድ ዩኤኢ አትቀበለውም ብሏል መግላጫው፡፡
ከዚህ በተጨማሪም መግለጫው ቱርክ ጽንፈኞችንና አሸባሪ ድርጅቶችን በመደገፍ አደገኛ ሚና እየተጫወተች ነው በማለት ኮንናለች፡፡
ዩኤኢ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አለምአቀፉ ማህበረሰብ የቱርክን እንቅስቀሴ በመጋፈጥ የቀጠናው ችግር እንዳይባባስ የበኩሉን ኃለፊነት መወጣት አለበት ብሏል፡፡