አረብ ኢምሬት ለአየር ንብረት ካሳ ክፍያ 100 ሚሊዮን ዶላር አዋጣች
በአየር ንብረት ለውጥ ለደረሱ ጉዳቶች ካሳ መክፈል የሚያስችል ፈንድ እንዲቋቋም ተወስኗል
28ኛው የተመድ አየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ በአረብ ኢምሬት ዱባይ መካሄድ ጀምሯል
አረብ ኢምሬት ለአየር ንብረት ካሳ ክፍያ 100 ሚሊዮን ዶላር አዋጣች።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በየዓመቱ በአየር ንብረት ለውጥ ዙሪያ የዓለም ሀገራት፣ የአየር ንብረት ለውጥ ባለሙያዎችን እና ሌሎች የሚመለከታቸውን አካላት ጋር ይመክራል፡፡
ይህ ጉባኤ በተመድ አባል ሀገራት እየተዟዟረ በየዓመቱ የሚካሄድ ሲሆን የዘንድሮው ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ከዛሬ ጀምሮ በተባበሩት አረብ ኢምሬት አስተናጋጅነት በዱባይ በመካሄድ ላይ ይገኛል፡፡
የአረብ ኢምሬት ኢንዱስትሪ እና ቴክኖሎጂ ሚንስትሩ ዶክተር ሱልጣን አልጃቢር የኮፕ ፕሬዝዳንትነትን ከኮፕ27 አዘጋጇ ግብጽ ውጪ ጉዳይ ሚንስትር ሳሜህ ሽኩሪ ተቀብለዋል።
ዶክተር ሱልጣን ፕሬዝዳንትነቱን በተቀበሉ በመጀመሪያው ዕለት የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳት እንዲመዘገብ እና ካሳ እንዲከፈል የሚያደርገውን የአየር ንብረት ለውጥ ፈንድ ማቋቋሚያ ረቂቅ ህግ እንዲያዘጋጅ አድርገዋል።
የተባበሩት አረብ ኢምሬት ለዚህ ፈንድ የሚሆን በቅድሚያ 100 ሚሊዮን ዶላር እንደምታዋጣ አስታውቃለች።
ዶክተር ሱልጣን በዚህ ጊዜ እንዳሉት የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳት ፈንድ እንዲቋቋም መደረጉ ለዓለማችን ትልቅ ድል ነው ብለዋል።
የአረብ ኢምሬት ውጪ ጉዳይ ሚንስትር ሼክ አብዱላህ ቢን ዛይድ አልናህያን በኤክስ አካውንታቸው " የዓለማችን ማህበረሰብ የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳት ፈንድ በመቋቋሙ እንኳን ደስ አላችሁ" ብለዋል።
በዚህ ጉባኤ ላይ የ200 ሀገራት መሪዎች ተገኝተዋል የተባለ ሲሆን ብሪታንያ 60 ሚሊዮን ፓውንድ ስተርሊንግ፣ ጀርመን 100 ሚሊዮን፣ አሜሪካ 17.5 ሚሊዮን እንዲሁም ጃፓን 10 ሚሊዮን ዶላር አዋጥተዋል።
የታዳጊ ሀገራት ቡድን መሪ የሆኑት ማደሊን ዲዩፍ በበኩላቸው የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳት ፈንድ እንዲቋቋም መወሰኑ ትልቅ ስኬት መሆኑን ተናግረዋል ።
ይህ ፈንድ የፊታችን ቅዳሜ በይፋ መመስረቱ የሚገለጽ ሲሆን በዓመት 100 ቢሊዮን ዶላር እንደሚዋጣ ይጠበቃል።
የዓለማችን ሀገራት ለዚህ ፈንድ የሚያዋጡት ገንዘብ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የሚደርሱ ጉዳቶችን በመለየት ካሳ እንዲከፈል ይደረጋል ተብሏል።
ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ ይተገበራል የተባለው ይህ የአየር ንብረት ለውጥ ፈንድ አሜሪካ የበለጸጉ ሀገራት ገንዘብ እንዲያዋጡ የሚያስገድድ ሊሆን አይገባም በሚል ተቃውሞዋን ገልጻለች።