የሀገራቱ ማእከላዊ ባንኮች ገንዘባቸው አሁን ባለው የመግዛት አቅም ልክ 46 ቢሊዮን ብር እና 3 ቢሊየን ድርሀም ለመቀያየር ተስማምተዋል
ኢትዮጵያ እና የተባበሩት አረብ ኤሜሬትስ በራሳቸው ገንዘብ ለመገበያየት የሚያስችላቸውን የመግባብያ ስምምነት ተፈራረሙ፡፡
ሀገራቱ ከአሜሪካን ዶላር ባለፈ እርስ በእርስ በሚያደርጓቸው ግብይቶች ብር እና ድርሀምን ለመጠቀም መስማማታቸውን ነው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ባወጣው መግለጫ ያስታወቀው።
ስምምነቱን የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ገዢ ማሞ ምህረቱ እና የተባበሩት አረብ ኤሜሬትስ ማዕከላዊ ባንክ ገዢ ካሊድ ሞሃመድ ባላማ ተፈራርመዋል።
ሀገራቱ በቀጣይ ዝርዝር አሰራሮች እና መመሪያዎች ላይ በጥልቀት የሚወያዩ ሲሆን ግብይቱን ለማሳለጥ ገንዘባቸው አሁን ባለው የመግዛት አቅም ልክ 46 ቢሊየን የኢትዮጵያ ብር እና 3 ቢሊየን የዩኤኢ ድርሀም በማከላዊ ባንኮቹ በኩል ለመቀያየር ተስማምተዋል።
ስምምነቱ አዲስ አበባ እና አቡዳቢ በጥሬ ገንዘብ ፍሰት፣ በፋይናንሻል ማርኬት እና በሌሎችም ኢኮኖሚያው ግንኙነቶች ጠንካራ ድንበር ተሸጋሪ ግብይት እንዲፈጽሙ የሚያስችላቸው ነው ተብሏል።
ብሄራዊ ብንኮቹ በሁለቱ ሀገራት መካከል የሚደረግ ግብይት በራሳቸው ገንዘብ እንዲከናወን ለማስቻል ባላቸው የንግድ ትስስር በኩል ይበልጥ ለማስተዋወቅ እና ለማሳደግ ተስማምተዋል።
ከዚህ ባለፈም በሁለቱም ሀገራት በኩል የሚገኙ የግል ባንኮች ትስስር እንዲፈጥሩ እና የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን ለማበረታታት ይህን ስምምነት ይበልጥ ጥቅም ላይ ለማዋል እንደሚሰራ ተገልጿል።
ሀገራቱ በራሳቸው ገንዘብ የሚያደርጉትን ግበይት ለመፈጸም እና ለመከተታተል የተባበሩት አረብ አሜሬቶች የኦንላይን የገንዘብ ማንቀሳቀሻ ዩኤኢ ስዊች እና የኢትዮጵያው ኢቲ ስዊች ጥቅም ላይ እንደሚውሉ ታውቋል።
በስምምነት ፊርማው ወቅት ንግግር ያደረጉት የዬኤኢ ማዕከላዊ ባንክ ገዢ ካሊድ ሞሃመድ ባላማ ስምምነቱ ሁለቱ ሀገራት በንግድ እና ኢንቨስትመንት ያላቸው ትብብር እያደገ መምጣቱን አመላካች ነው ብለዋል።
አክለውም ስምምነቱ ለባንክ እና ፋይናንስ ሴክተሩ ተጨማሪ የትብብር እድልን የሚከፍት እንደሆነ አመላክተዋል።
የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች የኢትዮጵያ አንዷ የንግድ አጋርና ከፍተኛ ቀጥተኛ የውጪ ኢንቨስትመንት ምንጭ ናት ያሉት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ በበኩላቸው፥ በኢትዮጵያ እየጨመረ የመጣውን የንግድ እና ኢንቨስትመንት ፍላጎት ምላሽ ለመስጠት የተለያዩ ሀገራት ገንዘቦችን ለመገበያያነት መጠቀም አማራጭን የሚሰፋ ነው ብለዋል።