ዚምባቡዌ በወርቅ የተደገፈ አዲስ የመገበያያ ገንዘብ ይፋ አደረገች
አዲሱ ገንዘብ “ዚግ” የሚል መጠሪያ ያለው ሲሆን “ዚምባቡዌ ጎልድ” ከሚል የተወሰደ ነው
ዚግ ገንዘብ በወርቅና ሌሎች ውድ ማእድናት መመንዘር የሚችል መሆኑ ተገልጿል
የዚምባቡዌ ማእከላዊ ባንክ በወርቅ የተደገፈ አዲስ የመገበያያ ገንዘብ በትናንትናው እለት ይፋ አድርጓል።
አዲሱ ገንዘብ “ዚግ ወይም ዚምባቡዌ ጎልድ” የሚል መጠሪያ የተሰጠው ሲሆን፤ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ለማረጋጋት እና ሰማይይ የነካውን የኑሮ ውድነት ለመቆጣጠር በማሰብ እንደታተመ ታውቋል።
የዚምባቡዌ ማእከላዊ ባንክ ዋና ገዢ ጆን ሙሻያቭንሁ፤ አዲሱ የመገበያያ ገንዘብ በየጊዜው የመግዛት አቅሙ እየተዳከመ የመጣውን የዚምባቡዌ ዶላር ይተካል ብለዋል።
የዚምባቡዌ ዜጎች በእጃቸው ላይ ያለውን የቀድሞውን የዚምባቡዌ ዶላር በ21 ቀናት ውስጥ ወደ አዲሱ የዚምባቡዌ ዚግ ገንዘብ ዚግ እንዲቀይሩም ባንኩ አሳስቧል።
በዚህ የገንዘብ ቅየራ ጊዜ አሁን ላይ በዚምባቡዌ ውስጥ በስፋ በጥቅም ላይ እየዋለ ባለው የአሜሪካ ዶላር መገበያየት ህጋዊ ሆኖ እንደሚቀጥልም ባንኩ አስታውቋል።
ከትናንት አርብ ጀምሮም በዚምባቡዌ ውስጥ የሚገኙ ባንኮች የቀድሞውን የዚምባቡዌ ዶላር በአዲሱ የዚምባቡዌ ዚግ የመቀየር ስራ መጀመራውንም የማእከላዊ ባንክ ዋና ገዢው አስታውቀዋል።
አዲሱ ዚግ ባለ 1, 2, 5, 10, 50, 100, እና 200 ኖቶች መታተሙንም ማእካለዊ ባንኩ አስታውቋል።
አዲሱ ገንዘብ “ዚግ ወይም ዚምባቡዌ ጎልድ” እንደ ከዚህ ቀደሙ የሀገሪቱ ገንዘብ ዋጋ እንዳያጣ በወርቅና ሌሎች ውድ ማእድናት መመንዘር የሚችል መሆኑን የሀገሪቱ ማእከላዊ ባንክ አስታውቋል።
የሃገሪቱ ብሔራዊ ባንክ ከዚህ ቀደም የተዳከመውን የሃገሪቱን ገንዘብ የመግዛት አቅም ለመታደግ በሚል የወርቅ ገንዘቦችን ህጋዊ አድርጎ ማተም እንደሚጀምር መግለጹ ይታወሳል።
"የወርቅ ሳንቲሞቹ በዓለም አቀፍ የወርቅ ዋጋ ላይ በመመስረት በተለያዩ የአገር ውስጥ ገንዘቦች እና በአሜሪካ ዶላር እንዲሁም በሌሎች የውጭ ምንዛሬ ገንዘቦዎች ጭምር ለሽያጭ እንደሚቀርቡም ነው የተነገረው።
ሳንቲሞቹ ከባለ 22 ካራት ወርቅ የሚዘጋጁ እንደሆነ እና ሳንቲሞቹን ለመለየት የሚያስችል ተከታታይ የቁጥር መለያ ኖሯቸው ይሰራሉም ተብሏል።