የአረብ ኤምሬትስ ፕሬዝዳንት ከግብጽ አቻቸው ጋር ተወያዩ
ፕሬዝዳንት ሞሃመድ ቢን ዛይድ ከአብዱልፈታህ ኤልሲሲ ጋር በሁለትዮሽና ቀጠናዊ ጉዳዮች ላይ መክረዋል
ግብጽና የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ጠንካራ የሁለትዮሽ እና ቀጠናዊ ትብብር አላችው
የአረብ ኤምሬትስ ፕሬዝዳንት ሼክ ሞሃመድ ቢን ዛይድ አል ናህያን ለይፋዊ ጉብኝት ግብጽ ገብተዋል።
ፕሬዝዳንቱ ካይሮ አለምአቀፍ አውርፕላን ማረፊያ ሲደርሱ በግብጽ አቻቸው አብዱልፈታህ ኤልሲሲ አቀባበል ተደርጎላቸዋል።
መሪዎቹ በኢትሃዲያ ቤተመንግስት ባደረጉት ምክክርም የሀገራቱን ጠንካራ ግንኙነት ማደስ የሚያስችል ውይይት ማድረጋቸውን ፕሬዝዳንት ሼክ ሞሃመድ ቢን ዛይድ አል ናህያን በትዊተር ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።
በተለይም የሀገራቱን የትብብር መስኮች ይበልጥ ማሳደግ የሚያስችል ምክክር መደረጉን ነው ፕሬዝዳንቱ ያነሱት።
በቀጠናው ሰላምና መረጋጋት ይሰፍን ዘንድም ኤምሬትስ ከግብጽ ጋር በትብብር በምትሰራባቸው ጉዳዮች ላይ ውይይት መደረጉን የአረብ ኤምሬትስ ዜና አገልግሎት ዘግቧል።
የግብጽ ፕሬዝዳንት አብዱልፈታህ ኤልሲሲ በየካቲት ወር 2023 በአቡዳቢ ጉብኝት ማድረጋቸው ይታወሳል።
አረብ ኤምሬትስ እና ግብጽ ጠንካራ ምጣኔ ሃብታዊ ግንኙነት እንዳላቸው መረጃዎች ያመላክታሉ።
በቀጠናዊ እና አለምአቀፍ መድረኮችም በጋራ ሲቆሙ ይታያል።
82 በመቶ የስንዴ አቅርቦቷን ከሩሲያ እና ዩክሬን በማስገባት የምትሸፍነው ግብጽ በጦርነቱ ምክንያት የምግብ እና የነዳጅ ዋጋ ንረት ገጥሟታል፤ የገንዘቧ ከዶላር አንጻር ያለው ዋጋም ከ50 በመቶ በላይ ቀንሷል።
የሀገሪቱ መንግስት 32 የመንግስት ኩባንያዎችን በከፊል ለግል ባለሃብቶች ለመሸጥ ማሰቡ ተነግሯል።
ከፕሬዝዳንት ሞሃመድ ቢን ዛይድ ር ወደ ካይሮ ያመሩ የኤምሬትስ ልኡካንም በዚሁ ጉዳይ ከግብጽ ባለስልጣናት ጋር እንደሚመክሩ ይጠበቃል ሲሉ የግብጽ መገናኛ ብዙሃን አስነብበዋል።