የሶሪያ ፕሬዝዳንት በሽር አል አሳድ በአረብ ኤምሬትስ ጉብኝት አደረጉ
አረብ ኤምሬትስ ሶሪያንና መንግስቷን ወደ ቀድሞው ሁኔታ መመለስ ያስፈልጋል ብላለች
በሽር አል አሳድ ባለፈው ዓመት የመጀመሪያውን የአረብ ሀገር ጉዟቸውን ወደ አረብ ኢሚሬትስ ማድረጋቸው ይታወሳል
የሶሪያ አረብ ሪፐብሊክ ፕሬዝዳንት በሽር አል አሳድ ለይፋዊ የስራ ጉብኝት እስከ ልዑካቸው አረብ ኤምሬትስ ገብተዋል።
ፕሬዝዳንት በሽር አል አሳድ አቡ ዳቢ ሲደርሱ የአረብ ኢሚሬትስ ፕሬዝደንት ሼክ መሀመድ ቢን ዛይድ አል ናህያን አቀባበል አድርገውላቸዋል።
የኤምሬትስ ተዋጊ ጄቶች የሶሪያውን ፕሬዝዳንት የያዘውን አይሮፕላን የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ የአየር ክልል ሲደርስ አጅበውታልም ተብሏል።
የኤምሬትስ ዜና አገልግሎት እንደዘገበዉ ፕሬዝዳንት አሳድን ለመቀበል 21 መድፍ ተተኩሷል።
ከፕሬዝዳንት በሽር አል አሳድ ጋር በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ግንኙነት ለማሳደግ ያለመ ገንቢ ውይይት መካሄዱን የአረብ ኢሚሬትስ ፕሬዝዳንት ሼክ መሀመድ ቢን ዛይድ በትዊተር ገጻቸው ላይ ተናግረዋል።
"ውይይታችን በሶሪያ እና በቀጠናው መረጋጋትን እና እድገትን ለማፋጠን ትብብርን የማጎልበት መንገዶችንም ዳሷል" ብለዋል።
አል አሳድ ባለፈው ዓመት መጋቢት ወር የተባበሩት አረብ ኤምሬትስን የጎበኙ ሲሆን፤ በፈረንጆች 2011 የሶሪያ የእርስ በርስ ጦርነት ከጀመረ በኋላ ወደ አረብ ሀገር ያደረጉት የመጀመሪያ ጉብኝት ነው።
የአረብ ኤምሬትስ ፕሬዝዳንት የዲፕሎማቲክ አማካሪ ዶ/ር አንዋር ጋርጋሽ ሶሪያን እና መንግስቷን ወደ ቀድሞው ሁኔታ መመለስ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
“የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች አቋም ሶሪያን ወደ ቀድሞ የመመለስ አስፈላጊነትን በተመለከተ ግልጽ ነው። ይህም ሼክ ሞሃመድ ቢን ዛይድ ከፕሬዚዳንት በሻር አል አሳድ ጋር ዛሬ ባደረጉት ውይይት አረጋግጠዋል” ብለዋል።