ሩሲያ እና ዩክሬን በኤምሬትስ አደራዳሪነት 200 የሚጠጉ ምርኮኞችን ተለዋወጡ
ሩሲያ 116 ዩክሬናውያን ምርኮኞችን የለቀቀች ሲሆን፥ ዩክሬን 63 ሩሲያውንን ለቃለች
የምርኮኞች ልውውጡ የተባበሩት መንግስታትን ሳያካተት በተባባሩት አረብ ኢሚሬትስ አሸማጋይነት ብቻ የተካሄደ ነው ተብሏል
በተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ ሸምጋይነት ሩሲያ እና ዩክሬን 200 የሚጠጉ ምርኮኞችን መለዋወጣቸው ተገለጸ።
ሩሲያ 116 ዩክሬናውያን ምርኮኞችን መልቀቋ ተገልጿል።
በምትኩ ዩክሬን 63 ሩሲያውንን መልቀቋን የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር አስታውቋል።
ይህ የሆነው የሩሲያ እና የዩክሬን ተወካዮች በህዳር ወር መጨረሻ ላይ የጦር ምርኮኞችን መለዋወጥ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ለመወያየት በተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ ተገናኝተው ከመከሩ በኃላ መሆኑን ነው ሮይተርስ ሶስት የመረጃ ምንጮቹን ጠቅሶ የዘገበው ።
ውይይቱ የተባበሩት መንግስታትን ሳያካተት በተባባሩት አረብ ኢሚሬትስ አሸማጋይነት ብቻ የተደረገ እንደነበርም ነው የተገለጸው፡፡
የሩሲያ የመከላከያ ሚኒስቴር ምርኮኞቹ በሩሲያ አየር ኃይል አማካኝት ወደ ሞስኮ ተወስደው አስፈላጊውን ህክምና እንዲያገኙና መልሰው እንዲቋቋሙ እንደሚደረግ አስታውቋል፡፡
ሚኒስቴሩ ባወጣው መግለጫ " የተደረገው ድርድርን ተከትሎ ህይወታቸው አደጋ ውስጥ ወድቆ የነበሩት የሩስያ ወታደሮች በኬቭ ጦር እጅ ካሉ ግዛቶች ተለቀው ተመልሰዋል” ብሏል፡፡
ዩክሬን እና ሩሲያ የምርኮኞች ልውውጥ ሲያደርጉ ይህ የመጀመሪያቸው አይደለም፡፡ በ 2023 መባቻ ላይ ከሁለቱም ወገን 100 የሚጠጉ ምርኮኞች ተለዋውጠው እንደነበር ይታወሳል፡፡
አረብ ኢሚሬትስ ከዩክሬን እና ሩሲያ በተጫማሪ ባሳለፍነው ወርሃ ታህሳስ በአሜሪካ እና ሩሲያ መካከል ለተደረገው የእስረኖች ልውውጥ የተጫወተችው ሚና ከፍተኛ እንደነበር አይዘነጋም፡፡
የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ ፕሬዝዳንት መሀመድ ቢን ዛይድ አል ነህያን ሁነኛ ሚና በተጫወቱበት ልውውጥ፤ ሩሲያ አሜሪካዊቷ የቅርጫት ኳስ ኮከብ ብሪትኒ ግሪነር ስትለቅ አሜሪካም “የሞት ነጋዴ” በመባል የሚታወቀውን ሩሲያዊ የጦር መሳሪያ አዘዋዋሪ ቪክቶር ቡትን የለቀቀችበት ታሪካዊ ስምምነት ነበር፡፡