ኤምሬትስ የሱዳንን ቀውስ ለማስቆም የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን እደግፋለሁ አለች
ፕሬዝዳንት ሼክ መሀመድ ቢን ዛይድ ከሱዳን ሉአላዊ ምክርቤት ሊቀመንበር ጀነራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን ጋር በስልክ ተወያይተዋል
ባለፈው አመት ሚያዚያ ወር የተጀመረው የሱዳን ጀነራሎች ፍልሚያ ሚሊየኖችን አፈናቅሎ ካርቱምን ለከባድ የሰብአዊ ቀውስ አጋልጧል
አረብ ኤምሬትስ የሱዳን ግጭት እንዲቆም የሚያስችሉ ሁሉንም አማራጮች እንደምትደግፍ አስታወቀች።
የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ሼክ መሀመድ ቢን ዛይድ በዛሬው እለት ከሱዳን ሉአላዊ ምክርቤት ሊቀመንበር ጀነራል አብዱልፈታል አልቡርሃን ጋር በስልክ ተወያይተዋል።
በውይይታቸውም ሱዳንን ከገባችበት ቀውስ በሚያስወጡ ጉዳዮች ላይ መነጋገራቸውን የኤምሬትስ ዜና ወኪል ዋም ዘግቧል።
ፕሬዝዳንት ሼክ መሀመድ ቢን ዛይድ በዚሁ ወቅት ለሰላማዊ ንግግር፣ ለሱዳናውያንን ፍላጎት፣ ደህንነት እና መረጋጋት ቅድሚያ መስጠት እንደሚገባ አሳስበዋል።
ኤምሬትስ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ለሚገኙ ሱዳናውያን የሰብአዊ ድጋፍ መላኳን እንደምትቀጥል በመጥቀስም ሁሉንም የሰላም አማራጮች እንደምትደግፍ ነው ፕሬዝዳንቱ ያነሱት።
ኦማር ሀሰን አልበሽርን ለመጣል የተባበሩት ጀነራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን እና ጀነራል ሃምዳን ዳጋሎ ልዩነታቸውን በንግግር ለመፍታት አለመፈለጋቸው በቋፍ ውስጥ የነበረውን የሱዳን ህዝብ ለከፋ ስቃይ መዳረጉን ቀጥሏል።
ባለፈው አመት ሚያዚያ ወር የጀመረው የጀነራሎቹ ፍልሚያ 48 ሚሊየን ህዝብ ያላትን ሱዳን በአለማችን ከባድ የሰብአዊ ቀውስ ውስጥ ካሉ ሀገራት ከቀዳሚዎቹ ተርታ አስቀምጧታል።
የመንግስታቱ ድርጅት በቅርቡ ባወጣው መግለጫ 26 ሚሊየን የሚጠጉ ሱዳናውያን ከፍተኛ የምግብ ዋስትና ችግር ገጥሟቸዋል ማለቱ የሚታወስ ነው።
የሱዳን ጦር እና የፈጥኖ ደራሽ ሃይሉ (አርኤስኤፍ) ጦርነት በንግግር እንዲቆም ሳኡዲ አረቢያ እና አሜሪካ በጂዳ ካደረጉትና በአጭሩ ከተቋጨው ሙከራ ውጭ እስካሁን ተስፋ ሰጪ ንግግር አልተካሄደም።
የምስራቅ አፍሪካ በይነ መንግስታት (ኢጋድ) እና የሱዳን ጎረቤቶች ተፋላሚ ጀነራሎቹን ፊት ለፊት ለማገናኘት ያደረጉት ሙከራም ሳይሳካ መቅረቱ ይታወቃል።
የመዲናዋን ካርቱም አብዛኛው ክፍል፣ አል ጀዚራ ግዛት፣ አብዛኛውን የዳርፉር እና ኮርዶፋን አካባቢ የተቆጣጠረው የፈጥኖ ደራሽ ሃይሉ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በምስራቅና ምዕራቡ የሀገሪቱ ክፍልም ድል እየቀናው መሆኑን በቅርቡ ቪኦኤ ይዞት የወጣው ዘገባ ማሳየቱ አይዘነጋም።
ሱዳናውያን ከ10 ሺህ በላይ ንጹሃንን ህይወት የቀጠፈውና ከ2 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑትን ደግሞ ከቀያቸው ያፈናቀለው ጦርነት እንዲቆም ተማጽኗቸውን ቀጥለዋል።