የሱዳን ተቀናቃኝ የፖለቲካ ኃይሎች በግብጽ ተገናኙ
የሱዳን ጦርነት ከ10 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ከቀያቸው እንዲፈናቀሉ፣ የረሀብ እና ብሔርን መሰረት ያደረጉ ግጭት አደጋዎች እንዲያንዣብቡ አድርጓል
በስብሰባው ወቅት ለሱዳን ጦር ውግንና አለው የተባለው የዲሞክራቲክ ብሎክ ከታቋደም ጋር የጋራ መግለጫ ለመስጠት ፍቃደኛ ሳይሆን ቀርቷል
የሱዳን ተቀናቃኝ የፖለቲካ ኃይሎች በግብጽ ተገናኙ።
የሱዳን ተቀናቃኝ የፖለቲካ ኃይሎች ጦርነቱ ከተጀመረ ከ15 ወራት ወዲህ ባለፈው ቅዳሜ በካይሮ በተካሄደ የእርቅ ንግግር ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ተገኝተዋል።
በስብሰባው ወቅት ለሱዳን ጦር ውግንና አለው የተባለው የዲሞክራቲክ ብሎክ ወይም ቡድን ለፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች ወግኗል ብሎ ከሚከሰው ታቋደም ጋር የጋራ መግለጫ ለመስጠት ፍቃደኛ ሳይሆን ቀርቷል። በዚህ ስብሰባ የሱዳን ጦርም ይሁን ፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች አልተገኙም።
ባለፈው አመት ሚያዝያ ወር የተጀመረው የሱዳን ጦርነት ከ10 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ከቀያቸው እንዲፈናቀሉ፣ የረሀብ እና ብሔርን መሰረት ያደረጉ ግጭት አደጋዎች እንዲያንዣብቡ አድርጓል። በሱዳን ሐተፈጸሙ ብሔርን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች አብዛኞቹ ጊዜ ፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች ተጠያቂ ሲደረጉ ይሰማል።
የፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች በዚህ ሳምንት ሲናርን ሲቆጣጠሩ አዲስ መፈናቀል ተከሰቷል። ለዚህ ምላሽ የሰጡት የሱዳን ጦር መሪ ጀነራል አልቡርሃን ከፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች እና ደጋፊዎቻቸው ጋር እንደማይደራደሩ ተናግረዋል።
"እየተባባሰ የመጣው የሰብአዊ ሁኔታ እና ያስከተለው አስከፊ ቀውሰ፣ ግጭቱ በአስቸኳይ እንዲቆም እንድንሰራ አስገድዶናል" ሲሉ አዲሱ የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ባድር አብደላቲ ተናግረዋል።
በአሜሪካ እና በሳኡዲ አረቢያ አመቻችነት በሱዳን ጦር እና በፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች መካከል በጂዳ ተጀምሮ የነበረው ድርድር ባለፈው አመት መጨረሻ ያለውጤት ተጠናቋል።
የቀድሞው የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክ በፕሬዝዳንትነት የሚመሩት ታቋደም የዲሞክራሲ ፓርቲዎች፣ የታጣቂ ቡድኖች እና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ጥምረት ነው። ሀምዶክ ታቋደም ለፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች ጦር ውግንና አለው የሚለውን ክስ አስተባለብዋል።
ለሱዳን ጦር ውግንና አለው የተባለው የዲሞክራቲክ ብሎክ ደግሞ በጦርነቱ እየተሳተፉ ያሉ የበርካታ ታጣቂ ቡድኖችን መሪዎች የሚያካትት ነው።
ታቋድም የሱዳን ጦርነት በሚቆምበት ሁኔታ በቅርቡ በአዲስ አበባ ውይይት ማድረጉ ይታወሳል።
ግብጽ ተጽዕኖዋን ተጠቅማ ቡድኖችን ለመሰብሰብ የቻለች ቢሆንም ዋና ተሳታፊዎቹ በስበሰባው መክፈታች በአዳራሹ በተቃራኒ አቅጣጫ ነበር የተቀመጡት።
ሁለቱ ቡድኖቹ የተስማሙት ጦርነቱ እንዲቆም ጥሪ የሚያቀርብ የጋራ መግለጫ የሚያወጣ ንኡስ ኮሚቴ ለማዋቀር ብቻ ነበር።
የሱዳን ጦር እና ፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች በሱዳን የጦር ወንጀል በመፈጸም አንዳቸው ሌላናቸውን እየከሰሱ ናቸው።