ኤሚሬትስ ኢትዮጵያን ጨምሮ በ12 ሀገራት ላይ የጣለችውን የጉዞ እግድ ከቅዳሜ ጀምሮ ልታነሳ ነው
እገዳው የተጣለው በኦሜክሮን የኮሮና ቫይረስ ቫሪያንት ምክንያት ነበር
ከኡጋንዳ፣ ከጋና እና ከሩዋንዳ የሚመጡ ተጓዦች ሶስቱን ምርመራች ማድረግ አለባቸው ተብሏል
የተባበሩት አረብ ኤሚሬትስ(ዩኤኢ) በኮሮና ቫይረስ መስፋፋት ምክንያት ኢትዮጵያን ጨምሮ በ12 የአፍሪካ ሀገራት ላይ ጥላው የነበረውን የጎዙ እግድ ልታነሳ መሆኑን አስታውቃለች፡፡
ኤሚሬትስ የጉዞ እግድ ጥላባቸው የነበሩት ሀገራት ኢትዮጵያ፣ኬንያ፤ደቡብ አፍሪካ ፤ናይጀሪያ፣ታንዛኒያ ፣ኮንጎ፤ቦትስዋና፣እስዋቲኒ፣ሌሴቶ፣ሞዛምፒክ፣ናሞቢያ እና ዚምባብዊ ናቸው፡፡
የእግዱ መነሳት ከቅዳሜ ጀምሮ ተግባራዊ ይሆናል ተብሏል፡፡
የሀገሪቱ የብሔራዊ የአደጋ ጊዜ ቀውስ እና የአደጋ ጊዜ መከላከል ባለስልጣን ባለፈው ረቡዕ መገባደጃ ላይ እንዳስታወቀው ባለፉት 14 ቀናት ውስጥ የተወሰኑ የአፍሪካ ሀገራትን በጎበኙ መንገደኞች ላይ ተጥሎ የነበረውን እገዳ ማንሳቱን አስታውቋል።
እገዳው የተጣለው በኦሜክሮን ቫሪያን ምክንያት መሆኑን ባለስልጣኑ ገልጿል፡፡
ከአፍሪካ ሀገራት የሚመጡ ተጓዦች ከመነሳታቸው ከ48 ሰአታት በፊት አሉታዊ የኮቪድ-19 PCR ምርመራ እና በመነሻ አየር ማረፊያ ሌላ ፈጣን የ PCR ምርመራ እንዲያቀርቡ ይጠበቃል።
መንገደኞች ሲደርሱ የኮቪድ-19 ምርመራ ይደረግባቸዋል ብሏል ባለስልጣኑ፡፡ከኡጋንዳ፣ ከጋና እና ከሩዋንዳ የሚመጡ ተጓዦች ሶስቱን ምርመራች ማድረግ አለባቸው ተብሏል፡፡