ሃገራቱ ለዓመታት ሻክሮ የዘለቀውን የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን ለማሻሻል እና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትን ለመጀመር መስማማታቸው የሚታወስ ነው
የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች በእስራኤል ቴልአቪቭ ኤምባሲዋን ለመክፈት ወሰነች፡፡
ኤሚሬትስ ይህን የወሰነችው የሃገሪቱ መንግስት ካቢኔ በተሰበሰበበት በዛሬው ዕለት ነው፡፡ ይህንንም የሃገሪቱ መንግስት በይፋዊ የትዊተር ገጹ አስታውቋል፡፡
ስብሰባው በምክትል ፕሬዝዳንት፣ጠቅላይ ሚኒስትር እና የዱባይ ገዢ ሼክ መሃመድ ቢን ረሺድ አል መክቱም የተመራው ነበር፡፡
ኤምባሲው ዩኤኢ በእስራኤል የሚኖራት የመጀመሪያው ዲፕሎማሲያዊ ተልዕኮ ነው የሚሆነው፡፡
ውሳኔው ለዓመታት ሻክሮ የዘለቀው የሃገራቱ ግንኙነት መሻሻሉን ተከትሎ የተወሰነ ነው፡፡ የ“አብርሃም” የሚል መጠሪያ የተሰጠውን ስምምነት "Abraham Accords" ተከትሎ ሃገራቱ የሁለትዮሽ ግንኙነቶቻቸውን ለማሻሻል እና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትን ለመጀመር መስማማታቸው የሚታወስ ነው፡፡
ስምምነቱ በተሰናባቹ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አግባቢነት ፈር ይዞ ለውጤት መብቃቱም አይዘነጋም፡፡ ትራምፕ ለመካከለኛው ምስራቅ እንደሚበጅ በማመን ያዘጋጁት የሰላም ዕቅድ ነበራቸው፡፡
የዩኤኢን ፈለግ ተከትለውም ሌሎች ባህሬይንን መሰል የቀጣናው ሃገራት ጎረቤት ሃገር ሱዳን ጭምር ከእስራኤል ጋር የነበራቸውን የሻከረ ግንኙነት አሻሽለዋል፡፡ ሳዑዲ አረቢያም ስለሁኔታው በማጤን ላይ ነች፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ የሚመራው የእስራኤል መንግስት የዩኤኢን ውሳኔ በጸጋ መቀበሉን አስታውቋል፡፡
የኔታንያሁ ቃል አቀባይ ኦፊር ገንደልማን “በቅርቡ በእስራኤል ወደሚከፈተው የኤሚሬትስ ኤምባሲ እንኳን በሰላም መጡ” የሚል ጽሁፍን በይፋዊ የትዊተር የማህበረሰብ የትስስር ገጽ አስፍረዋል፡፡
እስራኤል ኤምባሲ ለመክፈት የሚያስችላትን ጥያቄ ለኤሚሬት ማቅረቧንም የአል ዐይን አረብኛ ዘገባ ያመለክታል፡፡