አቡ ዳቢ ከፈረንጆቹ 2009 ጀምሮ በመካከለኛው ምስራቅ የአሜሪካ የወጪ ንግድ ቀዳሚ መዳረሻ ናት
በሰላምና ደህንነት፣ በቴክኖሎጂ እና ታዳሽ ሃይል ልማት ትብብራቸውን እያሳደጉ የሚገኙት አረብ ኤምሬትስ እና አሜሪካ የንግድ ልውውጣቸው በየአመቱ እየጨመረ ይገኛል።
የሀገራቱ የንግድ ልውውጥ ባለፈው የፈረንጆቹ አመት 2023 31.4 ቢሊየን ዶላር መድረሱም የዚህ ማሳያ ነው።
ኤምሬትስ በአሜሪካ በሪል ስቴት፣ ታዳሽ ሃይል ልማት እና ሌሎች ዘርፎች ያፈሰሰችው መዋዕለ ንዋይ 1 ትሪሊየን ዶላር መድረሱን በዋሽንግተን ዲሲ የሚገኘው የኤምሬትስ ኤምባሲ ያወጣው መረጃ ያሳያል።
ዋሽንግተንም በኤምሬትስ በኢነርጂ፣ ቴክኖሎጂ እና ፋይናንስ ገበያ የተሰማራች ሲሆን፥ ከ1500 በላይ ኩባንያዎቿ በአቡ ዳቢ በተለያዩ ዘርፎች ኢንቨስት አድርገዋል።
የዋሽንግተን እና አቡ ዳቢ የንግድ ትስስር ለ166 ሺህ አሜሪካውያን የስራ እድል የፈጠረ ሲሆን፥ ከ50 ሺህ በላይ አሜሪካውያንም በኤምሬትስ ይኖራሉ።
ከዛሬ ጀምሮ በአሜሪካ ይፋዊ ጉብኝት የሚያደርጉት ፕሬዝዳንት ሼክ መሀመድ ቢን ዛይድ ከ31 ቢሊየን ዶላር በላይ የደረሰውን የሀገራቱን የንግግድ ትስስር በሚያጠናክሩ ጉዳዮች ከፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ጋር ይመክራሉ።