በርካታ የግድያ ሙከራ የተደረገባቸው የአለም መሪዎች
በአሜሪካ አራት ፕሬዝዳንቶች በሰዎች ሲገደሉ አራት ፕሬዝዳንቶች ላይ ያልተሳኩ የግድያ ሙከራዎች ተደርገዋል
የቀድሞው የኩባ መሪ ፊደል ካስትሮ 638 የግደያ ሙከራዎችን ማምለጥ ችለዋል
የሰው ልጅ ከተበታተነ ስርአት ወጥቶ በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ በተማከል ስርአት መተዳደር ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ስልጣን እና አስተዳደራዊ በደሎችን መነሻ ያደረጉ በመሪዎች ላይ የሚቃጡ የግድያ ሙከራዎች ትላልቅ የታሪክ አካል ሆነው ቀጥለዋል፡፡
ከንጉሳውያን አስተዳደር አንስቶ በተደጋጋሚ የሚደርጉ የግድያ ሙከራዎች የታሪክ እጥፋት የተፈጸመባቸው የፖለቲካ አውድንም በመቀየር በኩል ያላቸው ሚና ቀላል የሚባል አይደለም፡፡
ህዝብን ለማስተዳደር በሰልጣን መንበር ላይ የሚቀመጡ መሪዎች በተለያየ ምክንያት ኢላማ የመሆናቸው እድል ከፍተኛ ነው፡፡
ሆኖም ሲበሉ ፣ ሲጠጡ ፣ ሲንቀሳቀሱ እና ህዝብ በተሰበሰበባቸው አካባቢዎች ሲገኙ የሚከተላቸው ከፍተኛ ጥበቃ ህይወታቸውን መታደግ ሳይችል የቀረበት እድል ለበርካታ ጊዜ ታይቷል፡፡
ገዳዮቹ ድርጊቱን ለመፈጸም ለረጅም ጊዜ በተጠና እቅድ መዘጋጀታቸው የግድያ ሙከራውን ድንገተኛ ስለሚያደርገው የጥበቃ ሀይሎችንም ንቃት የሚፈታተን ነው፡፡
በቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ላይ በወራት ልዩነት ለሁለት ጊዜ የተቃጣው የግድያ ሙከራ በአሜሪካ ፖለቲካዊ አመጽ ዳግም ሊያነግስ ይችላል በሚል ከፍተኛ ስጋትን አንዣቧል፡፡
የቀድሞው የኩባ መሪ ፊደል ካስትሮ በስልጣን ዘመናቸው በተቀናቃኞቻቸው የተቃጡ 638 የግድያ ሙከራዎችን በማምለጥ በታሪክ ለብዙ ጊዜ ሞትን በማምለጥ የሚጠቀሱ መሪ ናቸው፡፡
በአለም አስከፊ ከሚባሉ አምባገነኖች መካከል ቀዳሚ የሆነው አዶልፍ ሂትለር ከ 42 ጊዜ የግድያ ሙከራ አምልጦ በመጨረሻም የራሱን ህይወት በእጁ አጥፍቶ ምድርን ተሰናብቷል፡፡
ፈረንሳዊው ቻርልስ ደጎል ፣ ያሲር አረፋት እና ንግስት ቪክቶርያ በርካታ የግድያ ሙከራ የተቀጣባቸው መሪዎች በመሆን ከቀዳሚዎቹ ተርታ ተሰልፈዋል፡፡