የኤምሬትስ ፕሬዝዳንት የአሜሪካ ጉብኝት
ሼክ መሀመድ ቢን ዛይድ በዋይትሃውስ ከፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ጋር ይመክራሉ
አሜሪካ እና አረብ ኤምሬትስ 50 አመታትን የተሻገረ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አላቸው
የኤምሬትስ ፕሬዝዳንት ሼክ መሀመድ ቢን ዛይድ ከዛሬ ጀምሮ በአሜሪካ የመጀመሪያውን ይፋዊ ጉብኝት ያደርጋሉ።
ፕሬዝዳንት ሼክ መሀመድ ቢን ዛይድ በዋይትሃውስ ከአሜሪካ አቻቸው ጆ ባይደን ደማቅ አቀባበል ይደረግላቸዋል ተብሎ ይጠበቃል።
ሼክ መሀመድ ቢን ዛይድ የኤምሬትስ ፕሬዝዳንት ከሆኑ በኋላ ከባይደን ጋር ከዚህ ቀደም ስምንት ጊዜ የተገናኙ ሲሆን፥ በዋይትሃውስ የሚያደርጉት ምክክር ግን ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።
ኢኮኖሚና ንግድ፣ ኢንቨስትመንት፣ የታዳሽ ሃይል ልማት፣ የህዋ ምርምርና ቴክኖሎጂ፣ ሰው ሰራሽ አስተውሎት እና የአየር ንብረት ለውጥ ጥበቃ ዋነኛ አጀንዳዎች ይሆናሉም ተብሎ ይጠበቃል።
ኤምሬትስ በመካከለኛው ምስራቅ ቀጠና ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን እያደረገች ያለው ጥረትም ይመከርበታል ተብሏል።
የጋዛ እና ሱዳን ጦርነትን በንግግር ለማስቆም በሚደረጉ ሙከራዎች ላይም የኤምሬትስ እና አሜሪካ መሪዎች ውይይት ያደርጋሉ።