ኡጋንዳ የሚመሩትን ወታደር ትተው የሸሹ ወታደራዊ አዛዦችን አባረረች
አዛዦቹ በሶማሊያ ሰላም ማስከበር ተልዕኮ ላይ እያሉ በአልሻባብ ሲጠቁ ከመከላከል ይልቅ ራሳቸውን ለማዳን መሸሻቸው ተገልጿል
ባሳለፍነው ግንቦት አልሻባብ ከ50 በላይ የኡጋንዳ ወታደሮችን መግደሉ ይታወሳል
ኡጋንዳ የሚመሩትን ወታደር ትተው የሸሹ ወታደራዊ አዛዦችን አባረረች።
ምስራቅ አፍሪካዊቷ ሀገር ኡጋንዳ በአፍሪካ ህብረት ሰላም ማስከበር ተልዕኮ ስር ለሶማሊያ ወታደሮች ካዋጡ እና ከላኩ ሀገራት መካከል አንዷ ናት።
አልሻባብን ከሶማሊያ ለማጥፋት በሚልም ወደ ጎረቤት ሀገር ሶማሊያ የተላኩት የኡጋንዳ ወታደሮችም ከሌሎች የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ጦር ጋር እየሰሩም ይገኛሉ።
በደቡባዊ ሶማሊያ በሚገኘው ቡሎ ማሬር ካምፕ የሰፈረው የኡጋንዳ ጦር በኮለኔል ዲኦ አኪኪ እና ሜጀር ጀነራል ጆን ኦሉካ ይመራ እንደነበር ተገልጿል።
በሶማሊያ እና ሌሎች ሀገራት የሚንቀሳቀሰው አልሻባብ የተሰኘው የሽብር ቡድን ባሳለፍነው ግንቦት ወር ላይ በኡጋንዳ ሰላም አስከባሪዎች ላይ ጥቃት ሰንዝሮ በትንሹ 50 ወታደሮች ተገድለዋል።
ይህን የኡጋንዳ ጦር ይመሩ የነበሩት ሁለቱ አዛዦች የሚመሩት ጦር በአልሻባብ እየተጠቃ እያለ ጥቃቱን ማስቆም እያለባቸው ራሳቸውን ለማዳን እንደሸሹ ተገልጿል።
የኡጋንዳ ወታደራዊ ፍርድ ቤትም ሁለቱ ወታደራዊ አመራሮች ከውትድርና እንዲታገዱ እና ከሙያቸው እንዲባረሩ ሲል ውሳኔ ማሳለፉን ቢቢሲ ዘግቧል።
እነዚህ ወታደራዊ አዛዦች አልሻባብ ጥቃት ሊከፍትባቸው እንደሚችል አስቀድሞ መረጃ ደርሷቸው የነበረ ቢሆንም ጥቃቱን ከማስቆም ይልቅ ራሳቸውን ለማዳን እንደጣሩ በችሎቱ ወቅት ተጠቅሷል።
በአፍሪካ ህብረት ጥላ ስር የተሰማራው የሶማሊያ ሰላም አስከባሪ ጦር እስከሚቀጥለው ዓመት ድረስ ቀስ በቀስ ወታደሮቹን የማስወጣት እቅድ ተቀምጦለት እየተተገበረ ይገኛል።
አልሻባብ የሽብር ቡድን ከከተሞች የተገፋ ቢሆንም አብዛኞቹን የሶማሊያ ገጠር አካባቢዎች አሁንም ተቆጣጥሮ እንደያዘ ተገልጿል።