ፑቲንን መከላከል ካስፈለገ ኡጋንዳ ወታደሮቿን ወደ ሞስኮ ትልካለች -የኡጋንዳ ፕሬዝዳንት ልጅ
ሙሁዚ ካይኔሩጋባ ምዕራቡ ዓለም ጊዜውን በከንቱ የዩክሬን ፕሮፓጋንዳ ላይ እያጠፋ ነው ብለዋል
ኡጋንዳ በዩክሬን ግጭት ላይ በተባበሩት መንግስታት ምክረ-ሀሳብ ድምጽ ከመስጠት ተቆጥባለች
በሳለፍነው አርብ ምሽት የሩሲያው የቅጥረኛ ወታደር ቡድን ዋግነር ከዩክሬን ወደ ሩሲያ ገብቶ ሮስቶቭ የተሰኘችውን ከተማ አብዛኛው ክፍል መያዙን ተከትሎ በትናትናው እለት በሩሲያ ውጥረት ነግሶ ውሏል።
ዋግነር በመሪው ይቪግኒ ፕሪጎዥን በኩል የአመጽ ጥሪ ማስተላለፉን ተከትሎም በትናትናው እለት በሩሲያ ጦርና በዋግነር ቡድን መካከል ግጭቶች ተከትሰተው ነበር።
ይህንን ተከትሎም የኡጋንዳ መሪ ዩዌሪ ሙሴቬኒ ልጅ ሙሁዚ ካይኔሩጋባ የ"ኢምፔሪያሊስት" ስጋት ሲያጋጥም የኡጋንዳ ወታደሮች ሞስኮን እንደሚከላከሉ ተናግረዋል።
- የሩሲያ ጦርና የዋግነር ቡድን ግጭትን ተከትሎ ሀገራት ስለ ሁኔታው ምን አሉ?
- የኡጋንዳ ፕሬዝዳት ልጅ ጀነራል ሙሁዚ ኬኒሩጋባ ለአዲሷ የጣሊያን ጠ/ሚኒሰትር የጋብቻ ጥያቄ አቀረቡ
"ከፈለግክ የፑቲን አፍቃሪ ብለህ ጥራኝ፤ እኛ ኡጋንዳዊያን ሞስኮ በኢምፔሪያሊስቶች ስጋት ውስጥ ከወደቀች ወታደሮችን መላክ አለብን" በማለት በትዊተር ገጻቸው አስፍረዋል።
የቭላድሚር ፑቲን ጠንካራ ደጋፊ የሆኑት የፕሬዝዳንቱ ልጅ "ምዕራቡ ዓለም ጊዜውን በከንቱ የዩክሬን ፕሮፓጋንዳ ላይ እያጠፋ ነው" በማለትም አክለዋል።
በትዊተር ላይ አወዛጋቢ መግለጫዎችን መስጠት የሚታወቁት የ48 ዓመቱ ካይኔሩጋባ በዚህ ወር ለ2026 ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ እንደሚወዳደሩ አስታውቀዋል።
እ.አ.አ. በ2022 ዩዌሪ ሙሴቬኒ ልጃቸው ኬንያን ለመውረር መዛታቸውን ተከትሎ ስለሀገሪቱ ጉዳይ በትዊተር ሀሳብ እንደማይሰጡ አስታውቀዋል።
ኡጋንዳ በዩክሬን ግጭት ላይ በተባበሩት መንግስታት ድምጽ ከመስጠት ተቆጥባለች። ሩሲያ ዩክሬንን የወረረችበትን አንደኛ ዓመት አስመልክቶ ሞስኮ ወታደሮቿን ከሀገሪቱ እንድታስወጣ የሚጠይቀውን ድምጽም እንዲሁ።
በሰኔ ወር የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሰርጌ ላቭሮቭ አፍሪካን በጎበኙበት ወቅት፤ ካይኔሩጋባ ሩሲያን በመጥቀስ "እኛን የማይጎዳንን ሰው እንዴት እንቃወማለን? ብለዋል።
በአህጉሪቱ ከቅኝ ገዢዎች ጋር ይታገሉ የነበሩትን የነጻነት እንቅስቃሴዎችን በመደገፍ ሩሲያ ከአፍሪካ ጋር ጠንካራ ግንኙነት ነበራት።
ተንታኞች ሙሁዚ ካይኔሩጋባ የ78 አመቱ የአባታቸው ዩዌሪ ሙሴቬኒ ተተኪ እንደሆኑ አድርገው ይቆጥሯቸዋል።