የኡጋንዳ ምድር ሀይል አዛዥ ሌተናል ጀነራል ሙሁዚ ኬኒሩጋባ ከኃላፊነት ተነሱ
የፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቪኒ ልጅ የሆኑት ሙሁዚ ኬኒሩጋባ ከምድር ሀይል አዛዥ ከሀላፊነታቸው መነሳታቸው ተገለጸ
ሌተናል ጀነራል ሙሁዚ ኬኒሩጋባከ ኃላፊነት የተነሱት ያልተገባ ነገር በትዊተር ገጻቸው አጋርተዋል በሚል ነው
የኡጋንዳ ምድር ሀይል አዛዥ ሌተናል ጀነራል ሙሁዚ ኬኒሩጋባ ከኃላፊነት ተነሱ
የኡጋንዳ ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቪኒ የበኩር ልጅ የሆኑት ሌተናል ጀነራል ሙሁዚ ኬኒሩጋባ ከምድር ሀይል አዛዥነታቸው እንደተነሱ ቢቢሲ ዘግቧል።
እንደ ዘገባው ከሆነ የኡጋንዳ ምድር ሀይል አዛዡ ሌተናል ጀነራል ሙሁዚ ኬኒሩጋባ የእሳቸው እንደሆነ ሰማያዊ ባጅ ባለው የትዊተር ገጻቸው እሳቸው የሚመሩት ጦር ናይሮቢን ለመቆጣጠር ሁለት ሳምንት በቂ ነው ብለው ነበር።
የአዛዡን ትዊት ተከትሎም በርካቶች በጉዳዩ ዙሪያ ሃሳባቸውን በቀልድም በቁምነገርም የጻፉ ሲሆን ኬንያ ቅር መሰኘቷ ተገልጿል።
ይሄንን ተከትሎም ፕሬዝዳንት ዮሪ ሙሴቪኒ በልጃቸው ያልተገባ የትዊተር መልዕክት ምክንያት ማዘናቸው የተገለጸ ሲሆን ካለበት የምድር ሀይል አዛዥነት እንዳነሳቻው ዘገባው ጠቁሟል።
የኡጋንዳ አዛዥ የነበሩት ጀነራል ኬንሩጋባ የሙሉ ጀነራልነት ማዕረግ ተሰጥቷቸው የፕሬዝዳንቱ ልዩ ዘመቻዎች አማካሪ ሆነው መሾማቸውም ተገልጿል።
ጀነራል ሙሁዚ ኬኒሩጋባ የ78 ዓመቱን የኡጋንዳ ፕሬዝዳንት ዮሪ ሙሴቪኒን እንደሚተካ በተደጋጋሚ ቢገለጽም ጀነራሉ ግን በማህበራዊ የትስስር ገጾች የሀገሪቱን ዲፕሎማሲ እና ፕሮቶኮል የሚያበላሹ መልዕክቶችን በማጋራት ላይ ናቸው።
ከአንድ ወር በፊት በኢትዮጵያ ጉብኝት ያደረጉት ጀነራሉ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳዮች ዙሪያ በተለይም በሰሜን ኢትዮጵያ ስላለው ጦርነት፣ ሰለ ንጉስ ሚኒሊክ እና ሌሎች ጉዳዮች መልዕክታቸውን በትዊተር ገጻቸው በማሰራጨት ላይ መሆናቸውን ከትዊተር ገጻቸው ተመልክተናል።
ጀነራል ሙሁዚ ኬኒሩጋባ ከቀናት በፊትም በትዊተር ገጻቸው፤ “ትግራይ ሁሌም በልቤ አለች፤ ትግራይን መከላከል ከፈጣሪ የተሰጠኝ ትእዛዝ ነው ማለታቸው” ይታወሳል።