ፕሬዝዳንት ሙሴቪኒ “የዓለም ባንክ ባህላችንን እና ሀይማኖታችንን በገንዘብ እንድንቀይር እያስገደደን ነው” አሉ
ፕሬዝዳንቱ ኡጋንዳ ያለ ዓለም ባንክ እርዳታም ታድጋለች ብለዋል
ዓለም ባንክ ኡጋንዳ የተመሳሳይ ጾታ ጋብቻን በመከልከሏ ብድር እንደማይሰጥ አስታውቋል
ፕሬዝዳንት ሙሴቪኒ “የዓለም ባንክ ባህላችንን እና ሀይማኖታችንን በገንዘብ እንድንቀይር እያስገደደን ነው” አሉ።
ምስራቅ አፍሪካዊቷ ኡጋንዳ የተመሳሳይ ጾታ ጋብቻ የሚከለክል ህግ ማጽደቋን ተከትሎ በምዕራባዊያን ሀገራት ስትወገዝ ቆይታለች።
አሁን ደግሞ የዓለም ባንክ ለኡጋንዳ አዲስ ብድር እንደማይሰጥ ማስታወቁን ተከትሎ በርካታ ወገኖች ቁጣቸውን እየገለጹ ይገኛሉ።
ፕሬዝዳንት ዮሪ ሙሴቪኒ በበኩላቸው ኡጋንዳ ያለ ዓለም ባንክ ብድር ማደግ ትችላለች ብለዋል።
ፕሬዝዳንቱ አክለውም " የዓለም ባንክ እምነታችንን፣ ሉዓላዊነታችንን እን ባህላችንን በገንዘብ እንድንቀይር እያስገደደን ነው" ሲሉ ገልጸዋል።
ምዕራባዊያን "አፍሪካን ዝቅ አድርገው መመልከት እና ጫና ማሳደር ይፈልጋሉ፣ እኛ ችግራችንን እንዴት መፍታት እንዳለብን እናውቃለን፣ እነሱም የእኛ ችግሮቻችን ናቸው" ብለዋል።
ፕሬዝዳንቱ አክለውም ኡጋንዳ ከዓለም ባንክ ጋር ያለባትን ችግር ለመፍታት የሚቻል ከሆነ ውይይት ለማድረግ ትቀጥላለች ሲሉም ተናግረዋል ።
ኡጋንዳ ባሳለፍነው ግንቦት ወር ላይ የተመሳሳይ ጾታ ጋብቻን የሚከከለክል ህግን ያጸደቀች ሲሆን ፕሮዝዳንት ሙሴቪኒም ህጉ እንዲተገበር መፈረማቸው ይታወሳል።
ኣሜሪካ ኡጋንዳ ያጸደቀችውን ህግ ከመቃወም ባለፈ ማዕቀብ የጣለች ሲሆን አሁን ደግሞ የዓለም ባንክ ተጨማሪ ማዕቀብ ጥሏል።