አዲስ የባቡር መስመር መገንባት ያልቻለችው ኡጋንዳ መቶ ዓመት ያስቆጠረውን የባቡር መስመር ጠግና ልትከፍት ነው
ለ40 ዓመታት ያህል ከአገልግሎት ውጪ የሆነው የባቡር መስመር ወደ ነበረበት የመመለስ ስራ መጀመሩ ተነግሯል
ሀገሪቱ የረጅም ርቀት የጅምላ ጭነት ማጓጓዣን በጥቂት ዓመታት ውስጥ ከመንገድ ወደ ባቡር ለማዛወር ወጥናለች
ኡጋንዳ መቶ ዓመት ያስቆጠረውንና በብሪታኒያ የተሰራውን የባቡር መስመር ልትከፍት መሆኑን ተናገረች።
ወደ ደቡብ ሱዳን እና ዲሞክራሲያዊ ኮንጎ በማጓጓዝ ወጪን ይቀንሳል ተብሎ የሚጠበቀውን የባቡር መስመር ወደ ነበረበት መመለስ መጀመሩ ተነግሯል።
ለ40 ዓመታት ያህል ከአገልግሎት ውጪ የሆነው ይህ መስመር ከኬንያ የባህር ዳርቻ ሞምባሳ ወደብ የሚዘረጋው የምስራቅ አፍሪካ የባቡር መስመር አካል ነው።
መስመሩ በ20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጀመሪያ አካባቢ በኬንያ እና በኡጋንዳ የቀድሞ ቅኝ ገዥ ብሪታኒያ ተገንብቷል።
የኡጋንዳ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ቃል አቀባይ ጆን ሊንነን ሴንጌንዶ ለሮይተርስ እንደተናገሩት "ዓላማችን ሁሉንም የረጅም ርቀት የጅምላ ጭነት ማጓጓዣን በጥቂት ዓመታት ውስጥ ከመንገድ ወደ ባቡር ማዛወር ነው። ምክንያቱም ባቡር በርካሽ ገንዘብ እና በፍጥነት ማጓጓዝ እናገኛለን።"
ሀገሪቱ ዘመናዊና ደረጃውን የጠበቀ የባቡር መስመር የመገንባት እቅዷ ከቻይና ገንዘብ ማግኘት ባለመቻሉ የቀድሞውን መስመር ለማደስ ወስናለች።
በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ ኡጋንዳ ከቻይና ሃርቦር እና ኢንጂነሪንግ ኩባንያ ሊሚትድ ከተባለ ድርጅት ጋር የ2.2 ቢሊዮን ዶላር ዘመናዊ የባቡር መስመር ለመገንባት የነበራትን ውል አቋርጣለች።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ቻይና በኡጋንዳ መንግስት በቀረበው 55 ሚሊዮን ዶላር ገደማ ወጪ የቀድሞውን መስመር በሁለት ዓመታት ውስጥ እንደምታድስ ተናግሯል።
ጥገናው የሚካሄደው 382 ኪ.ሜ የባቡር መስመር ክፍል ላይ ሲሆን፤ ኬንያና ደቡብ ሱዳን ድንበር አጠገብ የሚገኙ የሎጂስቲክስ ማዕከላትን ያስተሳስራል።