የኡጋንዳ የጸጥታ አባላት ተቃዋሚዎች ላይ ከመጠን ያለፈ ኃይል እየተጠቀሙ ነውም ተብሏል
የኡጋንዳ ፖሊስ ህገ-ወጥ ተቃውሞ አድርገዋል ያላቸውን 11 ሴት የፓርላማ አባላትን ሀሙስ እለት በቁጥጥር ስር አውሏል።
አንዳንድ የህግ አውጪዎች በቁጥጥር ስር በዋሉበት ወቅት ጉዳት እንደደረሰባቸውም ተነግሯል።
የህግ አውጭዎቹ በዋና ከተማይቱ ካምፓላ ከሚገኙት የፓርላማ ህንጻዎች ወጣ ብሎ ወደ ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ሰልፍ ለማድረግ ሲዘጋጁ በቁጥጥር ስር ውለዋል።
ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ በሴት የህግ አውጭዎች የተዘጋጁ የተለያዩ ተግባራትን ለመበተን ፖሊስ ከፍተኛ ኃይል መጠቀሙን በመቃወም ነበር ሰልፍ የወጡት።
የፓርላማው ምክትል አፈ-ጉባኤ ቶማስ "በዛሬ ጠዋት ፖሊስ ሰላማዊ እና ትጥቅ ያልነበራቸውን 11 ሴት የፓርላማ አባላት ያሰረበትን መንገድ አጥብቄ አወግዛለሁ" ብለዋል።
የፖሊስ ቃል አቀባይ ሉክ ኦዎዬሲጊየር መኮንኖቹ ከመጠን ያለፈ ኃይል ተጠቅመዋል መባሉን አስተባብለዋል።
ህግ አውጭዎቹን በቁጥጥር ስር ለማዋል አንዳንድ የፖሊስ አባላትም ቆስለዋል ሲሉ ከሰዋል።
ህግ አውጭዎቹ በህገ ወጥ መንገድ ተቃውሞ ሲያደርጉ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ተናግረው በዋስትና መፈታታቸውንም ተናግረዋል።
ባለፉት ዓመታት የኡጋንዳ የጸጥታ አባላት በተለይም በአንጋፋው መሪ ዩዌሪ ሙሴቬኒ ተቃዋሚዎች ላይ ጭካኔ የተሞላበት ድርጊት ፈጽመዋል ሲል ሮይተርስ ዘግቧል።