የዓለም ፍጻሜ ደርሷል በሚል ወደ ኢትዮጵያ የገቡ ኡጋንዳዊያን ያንጋቶም እየኖሩ መሆኑ ተገለጸ
እነዚህ ኡጋንዳዊያን በደቡብ ሱዳን አድርገው ወደ ኢትዮጵያ እንደገቡ ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር አስታውቋል
በምስራቅ ኡጋንዳ አካባቢ የምጽዓት ቀን ደርሳል በሚል ሀብት እና ንብረታቸውን ሸጠው ወደ ኢትዮጵያ መሰደዳቸው ተገልጿል
ከኡጋንዳ የምጽዓት ቀን ደርሷል በሚል ወደ ኢትዮጵያ የመጡ ኡጋንዳዊያን በደቡባዊ ኢትዮጵያ ያንጋቶም እንዳሉ ተረጋግጣል።
ከወራት በፉት የዓለም ፍፃሜ ተቃርቧል በሚል ፍራቻ በኡጋንዳ ምስራቃዊ ክፍል በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከመንደራቸው ወጥተው ወደ ኢትዮጵያ መሰደዳቸውን የኡጋንዳ ፖሊስ ከሰሞኑ አስታውቆ ጉዳዩንም እየመረመረ መሆኑን ገልጾ ነበር።
ኡጋንዳዊያኑ "የክርስቶስ ሐዋሪያዎች" የተሰኘ እምነት ተከታዮች የዓለም ፍጻሜ በቅርቡ የሚጀምረው ከአካባቢያቸው መሆኑን በማመን ንብረታቸውን በመሸጥ ወደ ኢትዮጵያ በሕገወጥ መንገድ እየገቡ ያሉት ከየካቲት ጀምሮ እንደሆነ የኡጋንዳ ፖሊስ ተናግሯል ተብሏል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባዩ አምባሳደር መለስ አለም በሳምንታዊ መግለጫቸው ከሰሞኑ ከ100 በላይ ኡጋንዳዊያን የዓለም ፍጻሜ ደርሷል ፣መድህን የሚገኘውም በኢትዮጵያ ነው በሚል ወደ ኢትዮጵያ መጥተዋል ስለተባሉት የሀይማኖት ሰዎች ምላሽ ሰጥተዋል።
አምባሳደር መለስ እንዳሉት" በመቶዎች የሚቆጠሩ ኡጋንዳዊያን የዓለም ፍጻሜ ደርሳል፣ መዳኛችንም ኢትዮጵያ ነች በሚል ከሚኖሩበት ምስራቅ ኡጋንዳ ተነስተው በደቡብ ኢትዮጵያ በኩል ወደ ሀገር ውስጥ ገብተዋል፣ አሁን ላይ ያንጋቶም አካባቢ እንዳሉ ተረጋግጣል" ብለዋል።
ቃል አቀባዩ አክለውም ኢትዮጵያውያንን በህገ ወጥ መንገድ ወደ እስያ ሀገራት በአዲስ መንገድ የመውሰድ ሙከራ መጀመሩን ተናግረዋል ።
ኢትዮጵያውያንን ወደ ማንያማር እና ላኦስ በህገወጥ መንገድ ለመውሰድ ተሞክሮ ታይላንድ ላይ መያዛቸውን አምባሳደር መለስ አክለዋል።
ታይላንድ ላይ የተያዙትን ኢትዮጵያዊያን ጉዳይን ሕንድ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኢምባሲ እየተከታተለው እንደሆንም ቃል አቀባዩ ጠቅሰዋል።
ባለፉት 12 ወራት ውስጥም ከሳውዲ አረቢያ 125 ሺህ በአስቸጋሪ ሁኔታ ይኖሩ የነበሩ ዜጎችን ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ተደርገዋል ተብሏል።