ኡጋንዳዊው ባለስልጣን የ40 ዓመት እስር ተፈረደባቸው
የቀድሞ የሂሳብ ሰራተኛው ካዚንዳ የተፈረደባቸው ከበድ የሙስና ወንጀል ፈጽሟል በሚል ነው
የኡጋንዳ ፍርድ ቤት ካዚንዳን 26.4 ሚልዮን ዶላር ገንዘብ በማባከን ጥፋተኛ ናቸውም ብሏል
የኡጋንዳ ፍርድ ቤት ሙሰኛ ናቸው ባላቸው የሀገሪቱ ባልስለጣን የ40 ዓመታት የእስር ብይን አሳለፈ ፡፡
ፍርድ ቤቱ በትላንትናው ዕለት ባሳለፈው ብይን ቀደም ሲል በጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ውስጥ የሒሳብ ሰራተኛ ሆነው ሲያገለግሉ በነበሩ ጎድፍረይ ካዚንዳ ላይ ከ40 ዓመታት የእስር በተጨማሪ የ5.4 ሚልዮን ዶላር ቅጣት እንዲቀጡም ወስኗል፡፡
ጎድፍረይ ካዚንዳ በጦርነት ምክንያት ለተጎዳው የሀገሪቱ ሰሜናዊ ክፍል መልሶ ግንባት እንዲውል ከለጋሽ ድርጅቶች የተገኘው በሚልዮን ዶላሮች የሚገመት በጀት ለግል ጥቅም አውለዋል ብሏል ፍርድ ቤቱ፡፡
የቀድሞ የሂሳብ ሰራተኛው ለተመሳሳይ ዓላማ ከአየርላንድ፣ስዊድን እና ዴንማርክ የተገኘ 26.4 ሚልዮን ዶላር ገንዘብ አባክኗል በሚልም ጥፋተኛ ሆነው ተገኝቷል፡፡
የፍርድ ቤቱ ዳኛ ማርጋሬት ቲቡልያ “ካዚንዳ በሕገ -ወጥ መንገድ ራስን ማበልፀግ ፣ ማጭበርበር ፣ የገንዘብ ኪሳራ እና ወንጀሎችን ለመፈጸም ማሴር በሚሉ ክሶች ጥፋተኛ መሆናቸው ፍርድ ቤቱ አረጋግጠዋል” ብሏል፡፡
ተከሳሹ “19,171,476,505 ሽልንግ እንዲከፍሉ ታዝዘዋል” ሲሉም ተናግሯል ዳኛዋ በፍርድ ቤቱ።
1 ሚልዮን ዶላር የሚገመት የካዚንዳ መኖርያ ቤት እና 218ሺህ ዶላር የሚገመቱ ቅንጡ መኪኖቻቸውም በመንግስት እንዲወረሱ ተደርጓል፡፡
ካዚንዳ ለ10 ወራት ያህል በሸራተን ካምፓላ ውስጥ የመኖር ልምድ ያላቸው፣ ወደ ከፍተኛ ደረጃ የቱሪዝም መዳረሻዎችና በመላው ዓለም አዘውትረው የሚጓዙ እንዲሁም ቅንጡ ህይወት የሚኖሩ እንደሆኑም ይነሳል።
ፖሊስ በካምፓላ በሚገኙ የካዚንዳ ንብረቶች ባደረገው አሰሳ 273 ሺህ 700 ዶላር በካሽ መልክ ማግኘቱም ተገልጿል፡፡