የኡጋንዳው ፕሬዝዳንት ሙሴቬኒ በምስራቅ አፍሪካ “የፖለቲካ ፌደሬሽን ያስፈልጋል”ሲሉ በድጋሚ ጥሪ አቀረቡ
ሙሼቬኒ የስዋሂሊ ቋንቋን የመሳሰሉ"የጋራ ቅርሶች" ፌዴሬሽኑን ለመፍጠር ከፍተኛ ፋይዳ አላቸውም ብሏል
ፕሬዝዳንት ሙሴቬኒ የምስራቅ አፍሪካ ፌደሬሽን ጠንካራ ተሟጋች መሆናቸው ይታወቃል
የኡጋንዳው ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ፤ የምሰራቅ አፍሪካ የፖለቲካ እና ኢኮኖሚያዊ ውህደት ለማጠናከር “የፖለቲካ ፌደሬሽን” እውን ማድረግ እንደሚያስፈልግ ጥሪ አቀረቡ፡፡
ዩዌሪ ሙሴቬኒ ይህንን ያሉት ከታንዛንያ አቻቸው ሳሚያ ሱሉሁ ጋር በዳሬ-ሰላም ተገኝተው በሁለትዮሽ ጉዳዮች በሚመክሩበት ጊዜ ነው፡፡
የሀገራቱ መሪዎች የሁለትዮሽ ግንኙነቶቻን ለማጎልበት ጤና፣ንግድ እንዲሁም የምስራቅ አፍሪካ ድፍድፍ ዘይት ቧንቧ መስመር ፕሮጀክት (EACOP) ለምስራቅ አፍሪካ ማህበረሰብ ማቅረብን በተመለከቱ ጉዳዮች ላይ እንደመከሩም ነው የተገለጸው ።
በውይይቱ ስለ የ“ ምስራቅ አፍሪካ የፖለቲካ ፌደሬሽን” አስፈላጊነት ያነሱት ሙሴቬኒ፤ የፖለቲካ ፌዴሬሽን እውን ማድረግ ከተቻለ በምሰራቅ አፍሪካ በሚልዮን የሚቆጠሩ ስራዎች ከመፍጠር በዘለለ “የፌዴሬሽኑን አባል ሀገራት እንደ አሜሪካ፣ ቻይና፣ ዩናይትድ ኪንግደም እና የአውሮፓ ህብረት ካሉ ዋና ዋና የኢንዱስትሪ የንግድ አጋሮች ጋር የበለጠ የመደራደር አቅም እንዲኖራቸው የሚያስችል ነው” ብሏል።
ፕሬዝዳንቱ “ፌዴሬሽኑ እንደ ሶማሊያ፣ ሞዛምቢክ እና ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በመሳሰሉ ሀገራት ያለውን የጸጥታ ችግር ለማቃለል ያግዛል ሲሉም ነው የተናገሩት፡፡
ሙሴቬኒ የምስራቅ አፍሪካ መሪዎች በአካባቢው የሚገኙ ዋና ዋና ብሄረሰቦችንና እንደ የስዋሂሊ ቋንቋን የመሳሰሉ"የጋራ ቅርሶች" ፌዴሬሽኑን ለመፍጠር ያላቸውን ፋይዳ ከግምት ሊያስገቡ እንደሚገባም አሳስቧል፡፡
“ምስራቅ አፍሪካ በፖለቲካዊ (ፌዴሬሽን) እና በኢኮኖሚ (የጋራ ገበያ) ውህደት መልክ ከፍተኛውን አንድነት እንድገኝ የሚያስችሉት እነዚህ መመሳሰሎች እና ጥንታዊ ትስስሮች ናቸው"ም ብለዋል ሙሴቬኒ።
ሙሴቬኒ የተባበረ የፖለቲካ ፌደሬሽን መፍጠር ካልተቻለ፤ ለወደፊት የምስራቅ አፍሪካ ትውልዶች አሁን ላይ በአንዳንድ የዓለማችን ክፍሎች የሚስተዋሉ ችግሮች በዘላቂነት እንዲቀጥሉ የማድረግ ያክል ከባድ ነውም ብሏል፡፡
ሙሴቬኒ የምስራቅ አፍሪካ ፌደሬሽን ጠንካራ ተሟጋች ሲሆኑ ይህን መሰል ሀሳብ ከተነሳ ከአምስት አስርት አመታት በላይ ተቆጥሯል፡፡እንደፈረንጆቹ 2023 ፌዴሬሽኑ ተግባራዊ የሚሆንበት አዲስ ቀን ተብሎ ስምምነት ላይ ቢደረስም እስካሁን ድረስ በጉዳዩ ላይ ያለው እድገት አዝጋሚ ነው ተብሏል።