ዩክሬን በአንድ ሳምንት ውስጥ ሁለተኛውን የሩሲያ ቁልፍ ድልድይ አፈረስኩ አለች
ሩሲያ በበኩሏ በምስራቃዊ ዩክሬን ተጨማሪ ይዞታዎችን መቆጣጠሯን አስታውቃለች
ክሬምሊን ሩሲያ በቅርቡ በዶሃ ከዩክሬን ጋር ልትደራደር ነው በሚል የወጣውን ዘገባ ውድቅ አድርጓል
ዩክሬን በአንድ ሳምንት ውስጥ ሁለተኛውን የሩሲያ ቁልፍ ድልድይ ማፍረሷን ገለጸች።
የሀገሪቱ ጦር በሰይም ወንዝ ላይ የተገነባው የዝቫኖይ ድልድይ ተመቶ ሲፈርስ የሚያሳይ ቪዲዮ ለቋል።
የድልድዩ መፍረስ የሩሲያ ጦር እና የሎጂስቲክ እንቅስቃሴን በማወክ የኬቭ ጦር ግስጋሴን ያስቀጥላል ብለዋል የዩክሬን አየር ሃይል አዛዥ ሌተናል ጀነራል ማይኮላ ኦሌስቹክ።
ዩክሬን ባለፈው ሳምንት በጉልሽኮቮ ከተማ አቅራቢያ የሚገኘውን ድልድይ በተመሳሳይ መትታ ማፍረሷ ይታወሳል።
ፕሬዝዳንት ቮልድሚር ዜለንስኪ ትናንት ማምሻውን በሰጡት መግለጫ በሩሲያዋ ኩርስክ ክልል የሞስኮን ጥቃት ለመከላከል ጠንካራ ምሽግ እንደምትገነባ ተናግረዋል።
የሩሲያን ድንበር ጥሶ ከገባ ሁለተኛ ሳምንቱን የያዘው የሀገራቸው ጦር በሩሲያ ጦር ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱን በመጥቀስም “ዘመቻው” የሞስኮ የመልሶ ማጥቃት አቅም እስኪያልቅ ድረስ ይቀጥላል ብለዋል።
የፕሬዝዳንት ዜለንስኪ አማካሪ ሚካይሎ ፖዶልያክ በበኩላቸው ዩክሬን የሩሲያን ግዛት የመቆጣጠር ፍላጎት እንደሌላትና ዋነኛ ግቧ ሞስኮን ለድርድር ማስቀመጥ መሆኑን ገልጸዋል ብሏል ሬውተርስ በዘገባው።
የዩክሬን ጦርን ድንበር ጥሶ መግባት “ከባድ ጸብ አጫሪ ድርጊት ነው ያለችው ሩሲያ፥ ኬቭ እየፈጸመችው ለምትገኘው ጥቃት ዋጋ ትከፍልበታለች ስትል አስጠንቅቃለች።
ሞስኮ ግዛቷን ዘልቆ የገባውን የዩክሬን ጦር በፍጥነት ከማስወጣት ይልቅ በምስራቃዊ ዩክሬን ተጨማሪ ይዞታዎችን መቆጣጠርን የመረጠች ይመስላል።
ክሬምሊን ትናንት ባወጣው መግለጫ ከዩክሬን ጋር በዚህ ወር በኳታር መዲና ዶሃ ድርድር ሊደረግ ነው በሚል የወጣውን መግለጫ ውድቅ አድርጎታል።
ዋሽንግተን ፖስት ከትናንት በስቲያ ባወጣው ዘገባ ሁለቱ ሀገራት የኢነርጂ ተቋማትን ከጥቃት ለመጠበቅ የሚያስችል የተኩስ አቁም ስምምነት ለመድረስ ልኡካቸውን ይልካሉ ማለቱ ይታወሳል።
የዩክሬን ጦር በሩሲያ ግዛት ውስጥ የጀመረው ወረራ ግን የድርድር ሂደቱን እያስተጓጎለ ነው ብሎ ነበር።
የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ማሪያ ዛካሮቫ ግን ከዩክሬን ጋር በቀጥታም ይሆን በተዘዋዋሪ መንገድ ድርድር ለማድረግ የተጀመረ ጥረት አለመኖሩን ገልጸዋል።