የዩክሬን ጦር በሩሲያ ተጨማሪ ይዞታዎችን ተቆጣጥሮ ወደፊት እየገሰገሰ ነው - ዜለንስኪ
ፕሬዝዳንት ዜለንስኪ የሩሲያ ወታደሮችን ምርኮኛ ያደረጉ የሀገራቸውን ወታደሮችና አዛዦች አወድሰዋል
የዩክሬን ጦር በምዕራባዊ ሩሲያ ድንበር ጥሶ ከገባ ዛሬ 11ኛ ቀኑን ይዟል
የዩክሬን ጦር በሩሲያ ይዞታውን እያሰፋፋ ግስጋሴውን ቀጥሏል አሉ ፕሬዝዳንት ቮልድሚር ዜለንስኪ።
ፕሬዝዳንቱ በዛሬው እለት በሰጡት መግለጫ መጠናቸውን ያልጠቀሷቸው የሩሲያ ወታደሮች መማረካቸውን ተናግረዋል።
የዩክሬን ጦር አዛዥ ኦሌክሳንደር ሲይርስኪ በሩሲያ ተይዘው የነበሩ ዩክሬናውያን ወታደሮችና ንጹሃን ማስለቀቅ መቻሉን እንደነገሯቸውም ነው ዜለንስኪ የገለጹት።
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት በኩርስክ ክልል ጀብዱ እየፈጸሙ ነው ያሏቸውን የሀገራቸውን ወታደሮችና አዛዦች ማወደሳቸውን የሬውተርስ ዘገባ ያሳያል።
የዩክሬን ጦር በምዕራባዊ ሩሲያ ድንበር ጥሶ በመግባት ውጊያ ከጀመረ ዛሬ 11ኛ ቀኑን ይዟል።
እስካሁንም ወደ ሩሲያ ግዛት 35 ኪሎሜትር ዘልቆ በመግባት 115 ሺህ ሄክታር መሬት መቆጣጠሩን ነው ያስታወቀው።
ሩሲያ ከሁለተኛው የአለም ጦርነት ወዲህ የገጠማትን ከባድ ወረራ ለመግታት እርምጃ እየወሰደች መሆኑን ብትገልጽም እስካሁን በሙሉ አቅሟ እየተዋጋች አይደለም ተብሏል።
በዩክሬን በግዳጅ ላይ የተሰማሩና ልምድ ያላቸውን ወታደሮች በኩርስክ ክልል ለማሰማራት ትዕዛዝ ሰጥተዋል የተባሉት ፕሬዝዳንት ፑቲን ኬቭ ከባድ ዋጋ እንደምትከፍል መዛታቸው ይታወሳል።
ክሬምሊን የዩክሬን ጦር እየፈጸመው ባለው ወረራ የምዕራባውያንን የጦር መሳሪያዎች እየተጠቀመ መሆኑን ገልጿል።
በትናንትናው እለት በኩርስክ ክልል ትልቁ ድልድይ ተመትቶ የፈረሰው በአሜሪካ ሰራሹ ሂማርስ ሮኬት መሆኑንም ይፋ አድርጓል።
ሩሲያ ድንበሯን ዘልቆ ጥቃት ለከፈተው የዩክሬን ጦር ፈጣን ምላሽ ከመስጠት ይልቅ ተጨማሪ የዩክሬን ከተሞችን ለመቆጣጠር ጥረት እያደረገች መሆኑን ፍራንስ 24 አስነብቧል።
ሞስኮ በዶኔስክ ግዛት ፖክሮስቭስክ እና ቶሬትስክ የተባሉ ከተሞችን ለመቆጣጠር እየገሰገሰች ነው ያለችው ኬቭ ዜጎቿ ከአካባቢዎቹ በፍጥነት ለቀው እንዲወጡ አሳስባለች።