ዩክሬን በኩርስክ ግዛት እያካሄደች ባለችው ጥቃት ቁልፍ ድልድይ አወደመች
የዩክሬን ሀይሎች በምዕራብ ሩሲያ ወደፊት መግፋታቸውን ቢገልጹም፣ የሩሲያ ኃይሎችም በመሳሳይ በምስራቅ ዩክሬን ተጨማሪ ቦታዎችን እየያዙ ነው ተብሏል
ዩክሬን በሩሲያ ኩርስክ ግዛት ጥሳ በመግባት እየፈጸመችው ያለው ጥቃት አሁን ሁለተኛ ሳምንቱን አስቆጥሯል
ዩክሬን በኩርስክ ግዛት እያካሄደች ባለችው ጥቃት ቁልፍ ድልድይ አወደመች።
ዩክሬን በሩሲያ ኩርስክ ግዛት ጥሳ በመግባት እየፈጸመችው ያለው ጥቃት አሁን ሁለተኛ ሳምንቱን አስቆጥሯል።
ዩክሬን በፈጸመችው በዚህ ድንገተኛ ጥቃት 120ሺ ሰዎች ከቀያቸው እንዲፈናቀሉ አስገድዷል። ዩክሬን በኩርስክ ግዛት ተጨማሪ ቦታዎችን መያዟን እየገለጸች ቢሆንም፣ ሩሲያን የመውረር ፍላጎት እንዳልነበራት በተደጋጋሚ ተናግራለች።
"ዩክሬን የሩሲያን ግዛት የመውረር ፍላጎት የላትም" ሲሉ የዩክሬኑ ፕሬዝደንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ ከፍተኛ አማካሪ አርብ እለት ተናግረዋል።
አማካሪው ማይካይሎ ፖዶሊያክ ሩሲያን ግዛት የመውረር ቁልፉ አላማው ሞስኮ "እኛ ባስቀመጥነው ቅድመ ሁኔታ" እንድትደራደር ማድረግ ነው ብለዋል።
"በኩርስክ ግዛት ሩሲያ ፍትሀዊ ወደ ሆነ ድርድር እንድትመጣ ወታደራዊ አማራጭ እንዴት ጥቅም ላይ እንደሚውል አይተናል" ሲሉ በኤክስ ገጻቸው የገለጹት አማካሪው አክለውም ኪቭ "ውጤታማ የማስገደጃ ዘዴ" ምን እንደሆነ አረጋግጣለች ብለዋል።
የዩክሬኑ ኢታማዦር ሹም ኦሌክሳንደር ሲይርስኪ የማጥቃት ዘመቻው መሻሻል እያሳየ ነው ብለዋል። "በማጥቃት ላይ ያሉት ወታደሮች እየተዋጉ መሆናቸውን እና በአንድ አንድ ቦታዎች ከአንድ እስከ ሶስት ኪሎሜትር ወደ ጠላት መጠጋታቸውን" በማህበሪዊ ሚዲያ በተለቀቀ ቪዲዮ ሲርስኪ ለዘለንስኪ ሲናገሩ ተደምጠዋል።
ሲርስኪ ከድንበር 13 ኪሎሜትር ላይ በምትገኘው ማላ ሎክንያ መንደር አቅራበመያ እየተደረገ ባለው ውጊያ "ብዙ እስረኞችን" እንደሚያስለቅቁ ተስፋ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
ዩክሬይን ወደ ፊት እየገፋች ሲሆን ከዩክሬን ጋር ድንበርተኛ የሆነችው የሩሲያዋ ቤልጎሮድ ባለስልጣናት ከሰኞ ጀሞሮ የአምስት መንደሮች ነዋሪዎችን እንደሚያስወጡ እየተናገሩ ናቸው።
የዩክሬን ሀይሎች በምዕራብ ሩሲያ ወደፊት መግፋታቸውን ቢገልጹም፣ የሩሲያ ኃይሎችም በመሳሳይ በምስራቅ ዩክሬን ተጨማሪ ቦታዎችን እየያዙ ነው ተብሏል። በትናንትናው እለት ሞስኮ ወታደሮቿ ሰርሂቪካ የተባለች ከተማ መያዛቸውን ገልጻለች።
በቅርቡ የተያዙት ቦታዎች፣ የሩሲያ ኃይሎች የዩክሬን ኃይሎች እንደ ሎጂሴቲክ ማዕከል ወደሚጠቀሙባት ፖክሮቭስክ ከተማ እንዲቀርቡ አስችሏቸዋል። ፖክሬቭስክ በሩሲያ ቁጥጥር ስር ካለው የዶኔስክ ግዛት በሰሜን ምዕራብ የሚገኝ ከተማ ነው።
የከተማ ዋና አስተዳዳሪ የሆኑት ሰርጌ ዶብሪያክ ባስተላለፉት መልእክት የሩሲያ ኃይሎች ወደ ከተማዋ ዳርቻዎች እየመጡ ስለሆነ ህዝብ እንዲወጣ አሳስበዋል።
ዩክሬን እስካሁን በኩርስክ ግዛት እየፈጸመች ባለው ጥቃት ከአንድ ሺ ስኩየር ኪሎሜትር በላይ ስፋት ያለው መሬት መቆጣጠሯን ገልጻለች።
ጥቃቱን አደገኛ ትንኮሳ ሲሉ የገለጹት ፑቲን በኩርስክ ግዛት የገባው ኃይል እንዲደመሰስ ትዕዛዝ ማስተላለፋቸው ይታወሳል።