ሩሲያ በኒዩክሌር ሃይል የምትስራ መርከቧን ወደ አርክቲክ ላከች
መነሻዋን ሴቨርዶኔስክ ያደረገችው መርከብ 16 የኒዩክሌር አረር መሸከም የሚችሉ ሚሳይሎችን መታጠቋም ተገልጿል
ሞስኮ የጦር መርከቦቿን በዘመናዊና አነስተኛ መርከቦች እየተካች ነው ተብሏል
በኒዩክሌር ሃይል የምትንቀሳቀሰው የሩሲያ ዘመናዊ መርከብ ወደ አርክቲክ ጉዞ መጀመሯ ተነገረ።
በሩሲያው የቀድሞ ጀነራል ሱቮሮቭ ስም የተሰየመችው “ጄነራሊሲሞ ሱቮሮቭ” የጦር መርከብ በትናንትናው እለት ጉዞ መጀመሯን ታስ የዜና ወኪል አስነብቧል።
መነሻዋን ሴቨርዶኔስክ ያደረገችው መርከብ 16 የኒዩክሌር አረር መሸከም የሚችሉ ሚሳኤሎችን መታጠቋንም ዘገባው አክሏል።
መርከቧ በ2022 በፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ትዕዛዝ የሩሲያን ባህር ሃይል መቀላቀሏ የሚታወስ ነው።
ሞስኮ በኒዩክሌር ሃይል የሚሰሩ መርከቦችን በስፋት እያመረተች ትገኛለች የሚለው ሬውተርስ፥ እነዚህ መርከቦች በነዳጅ ከሚሰሩት ይልቅ ፈጣን መሆናቸውን ያብራራል።
“ጄነራሊሲሞ ሱቮሮቭ” የኒዩክሌር አረር መሸከም የሚችሉ ሚሳኤሎችም ታጥቃ ነው ወደ አርክቲክ እየተጓዘች ያለችው።
የጉዞዋ ዋነኛ አላማ ባይጠቀስም በዩክሬን ጦርነት ከምዕራባውያን ጋር ቁርሾ ውስጥ ያለችው ሞስኮ፥ በአርክቲክ ደህንነቷን ለማስጠበቅ የወሰደችው እርምጃ ሊሆን ይችላል ተብሏል።
በአዲስ አመት መልዕክታቸው ምዕራባውያንን በጠላትነት የፈረጁት ፑቲን፥ ሃይፐርሶኒክ ሚሳኤሎችን የታጠቀች መርከብን በቅርቡ ወደ አትላንቲክ ውቅያኖስ ማሰማራታቸው የሚታወስ ነው።
ሞስኮ በባህር ውስጥ የሚምዘገዘግ ኒዩክሌር ተሸካሚ “ቶርፒዶ” የጦር መሳሪያዋም ከአሜሪካ ጋር አፋጧታል።