ጀርመንና አሜሪካ የውጊያ ተሽከርካሪዎችን ወደ ዩክሬን ሊልኩ ነው
ጆ ባይደን "ዩክሬናውያንን ለመርዳት የምንችለውን ሁሉ ማድረግ አለብን" ሲሉ ተናግረዋል
የዩክሬን ፕሬዝዳንት "ጀርመን የሩስያ ሚሳኤሎችን ለመጥለፍ ትልቅ አስተዋጸኦ እያበረከተች ነው" ብለዋል
የአሜሪካ እና የጀርመን መሪዎች ኪቭ የሩሲያ ጦር ለመመከት ያስችላት ዘንድ የጦር መሳሪያዎችን ወደ ዩክሬን እንደሚልኩ አስታውቀዋል፡፡
በፕሬዝዳንት ጆ ባይደን እና በመራሄ መንግስት ኦላፍ ሾልዝ መካከል የተደረገውን የስልክ ውይይት ተከትሎ የወጣው የጋራ መግለጫ እንደሚያመላክተው ሀገራቱ የውጊያ ተሽከርካሪዎችን ወደ ዩክሬን ይልካሉ፡፡
ቢዘህም መሰረት አሜሪካ ለዩክሬን የምታደርገው የ2.8 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ አካል የሆነው የ50 ተዋጊ ተሸከርካሪዎች እንዲሁም ጀርመን የፓትሪዮት አየር መከላከያ ባትሪን ለዩክሬን ድጋፍ እንደምያደረጉ ሮይተርስ አንድ የአሜሪካ ከፍተኛ ባለስልጣን ጠቅሶ ዘግቧል፡፡
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን "አሁን በዩክሬን ያለው ጦርነት አሳሳቢ ደረጃ ላይ ነው፤ ስለዚህም ዩክሬናውያን የሩስያ ጥቃትን ለመቋቋም እንዲረዳቸው የምንችለውን ሁሉ ማድረግ አለብን" ሲሉ መናገራቸውም ነው የተገለጸው፡፡
ሁለቱም ሀገራት የዩክሬን ወታደሮችን መሳሪያዎቹን እንዴት መጠቀም እንዳለባቸውም ጭምር ለማሰልጠን ተስማምተዋል፡፡
በመልሶ ማጥቃት ድል እየተቀዳጀች መሆኑን የሚነገርላት ዩክሬን የሩሲያን መጠነ ሰፊ ዘመቻ ለመመከት ከዓለም አቀፍ አጋሮቿ ተጨማሪ ድጋፍ እንዲደደረግላት በተደጋጋሚ ጥሪ ስታደርግ መቆየቷ አይዘነጋም፡፡
በዩክሬን ምድር ያለውን ከባድ ቀውስ ከግምት ያስገቡት ፕሬዝዳንት ባይደን እና መራሄ መንግሰት ሾልዝ ለዩክሬን የሚያደርጉትን አስፈላጊውን የገንዘብ፣ የሰብዓዊ፣ ወታደራዊ እና ዲፕሎማሲያዊ ድጋፍ አጠናክረው ለመቀጠል ያላቸውን የጋራ ቁርጠኝነት ገልጸዋል፡፡
የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎዶሚር ዘሌንስኪ "ጀርመን ሁሉንም የሩስያ ሚሳኤሎችን ለመጥለፍ ትልቅ አስተዋጸኦ እያበረከተች ነው!" ሲሉ ለጀርመን አስተዋጽዖ ያላቸውን አድናቆት በትዊተር ገጻቸው አስፍረዋል፡፡
ውሳኔው የተገለጸው ፈረንሳይ ቀላል ኤ.ኤም ኤክስ-10 አር.ሲ የታጠቁ የጦር ተሽከርካሪዎችን እንደምትልክ ካሳወቀችና የሾልዝ መንግስት ለሀገሪቱ የሶስትዮሽ ጥምረት ለዩክሬን ወታደራዊ ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ ካቀረቡ በኋላ ነው።
ጀርመን በሩሲያ- ዩክሬን ጦርነት ጉዳይ የክሬምሊን ባለስልጣናት ተጠያቂ መሆናቸው ስትገልጽ የነበረ ቢሆንም ፤ እንደ ሌሎች የአውሮፓ ሀገራት መሰል የጦር መሳሪያዎች ለዩክሬን በድጋፍ መልክ ስትሰጥ የመጀመሪያ ነው ተብሏል፡፡