አዲሱ የብር ኖት በጦርነቱ የተፈጸሙ ወንጀሎች እና የዩክሬናውያን ተጋድሎ የሚያመላክቱ ምስሎች ያለበት ነው
የዩክሬን ማዕከላዊ ባንክ አንድ አመት የሆነውንና ዩክሬን “የሩሲያ ወረራ” እያለች የምትጠራውን ጦርነት መታሰቢያ የሚሆን የብር ኖት ይፋ አድርጓል፡፡
ይፋ በተደረገው የገንዘብ ኖት በአንዱ ገጽ ላይ በጦርነቱ የተፈጸሙ ወንጆሎች የሚገልጹ ሁለት የታሰሩ እጆች እንዲሁም በሌላኛው ሶስት ወታደሮች ብሄራዊ ሰንደቅ አላማ ሲያወለብልቡ የሚያሳይ ምስል ያለበት ነው፡፡
የዩክሬን ብሔራዊ ባንክ ገዥ አንድሪይ ፒሽኒ “የጦርነቱን አንደኛ አመት ለማክበር በትንሽ ወረቀት ላይ የአንድ አመት ስሜትን ፣ስርአትን ፣ይዘትን እና ምስላዊ ነገሮችን የሚያሳይ የመታሰቢያ የገንዘብ ኖት ይፋ ለማድረግ ወሰንን” ሲሉ ተናግረዋል።
አዲስ ኖት 300ደ ሺህ ስርጭት ይኖረዋልም ብለዋል ፒሽኒ።
"በዚህ አመት ውስጥ ዩክሬናውያን ያላቸውን ኃይል፣ አስፈላጊነታቸው፣ የተቃጣባቸውን አደጋ መቋቋም ብቻ ሳይሆን ለተፈጸመው ወንጀል ይቅር ሳይሉ ምላሽ በመስጠት ማሸነፍ እንደሚችሉ ተገንዝበዋል” ያሉት የዩክሬን ብሔራዊ ባንክ ገዥ አንድሪይ ፒሽኒ ፤ ድሉ ለዩክሬናውያን ትልቅ ዋጋ ያለው መሆኑም ገልጸዋል፡፡
ኖቱን ለማዘጋጀት ስምንት ወራት ያህል እንደፈጀም ነው ሮይተርስ የዘገበው፡፡
የባንኩ ኃላፊዎች ጦርነቱን የሚያሳዩ ምስሎች ያሉባቸው ተከታታይ የዩክሬን የብር ኖቶች (ሂሪቪንያ ) የማዘጋጀት እቅድ እንዳላቸውም አስታውቀዋል፡፡
በጦርነቱ የተገኙ ድሎችን የሚያስታወሱና እና የዩክሬንን መልሶ ግንባታ የሚያመላክቱ አዳዲስ የብር ኖቶች ከወዲሁ ማዘጋጀት መጀመራቸውንም ነው የገለጹት ኃላፊዎቹ፡፡
የዩክሬን ማዕከላዊ ባንክ ባለፈው አመት የካቲት 24 ቀን ሩሲያ በሀገሪቱ መጠነ ሰፊ ወታደራዊ ዘመቻ መጀመሯን ተከትሎ ኢኮኖሚውን ለማቆየት እና መረጋጋትን ለመፍጠር ሲታትር የቆየ ተቋም መሆኑ ይነገራል፡
የባንኩ ጥረት በምዕራባውያን አጋሮች ከሚደረገው የቢሊዮን ዶላር ድጋፍ ጋር ተዳምሮ አሁን ላይ የዩክሬን የምንዛሪ ክምችት ወደ 30 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ሲሆን ይህም ጦርነቱ ከተጀመረበት ጊዜ ትንሽ ከፍ ያለ ነው ተብሏል፡፡
ሩሲያ በዩክሬን ላይ ወታደራዊ ዘመቻ ከጀመረች ዛሬ ድፍን አንድ አመት ሆኗታል፡፡