የሩስያ መከላከያ ሚኒስቴር የዩክሬን ጦር በሉሃንስክ ክልል ወደ ኋላ ማፈግፈጉን ገልጿል
ሩሲያ በዩክሬን ምስራቃዊ ክፍል ሁለት የመከላከያ መስመሮችን ሰብሬያለሁ ብላለች።
ምዕራባውያን አጋሮች ደግሞ ኬቭ ለመልሶ ማጥቃት እየተዘጋጀች ባለችበት ወቅት ወታደራዊ እርዳታን ለማጠናከር ቃል ገብተዋል።
በታህሳስ ወር በአስር ሺዎች በሚቆጠሩ ተጠባባቂ ኃይሎች የተጠናከረችው ሩሲያ ባለፉት ሳምንታት በደቡባዊና ምስራቃዊ ዩክሬን ጥቃቶችን አጠናክራለች።
የጦርነቱ አንደኛ ዓመት ሲቃረብም ትልቅና አዲስ ጥቃት ይጠበቃል ተብሏል።
የዩክሬን ምክትል መከላከያ ሚኒስትር ሃና ማሊያር "በምስራቅ በኩል የጠላት ጥቃት ቀንና ሌሊት ቀጥሏል" ብለዋል።
በቴሌግራም ባስተላለፉት መልዕክታቸው "ሁኔታው አስጨናቂ ነው። ነገር ግን ተዋጊዎቻችን ጠላት ግቡን እንዲያሳካ አይፈቅዱም። በጣም ከባድ ኪሳራ እያደረሱ ነው" በማለት ወቅታዊ ሁኔታውን ገልጸዋል።
የሩስያ መከላከያ ሚኒስቴር በበኩሉ የዩክሬን ጦር በሉሃንስክ ክልል ወደ ኋላ ማፈግፈጉን ገልጿል፤ ምንም እንኳን ሚንስቴሩ ዝርዝር መረጃ ባይሰጥም።
ሮይተርስ ይህንን እና ሌሎች የጦር ሜዳ ሁነቶችን ማረጋገጥ እንዳልቻለ ዘግቧል።
ሞስኮ የዩክሬን "የተጠናከረው ሁለተኛው የጠላት የመከላከያ መስመር እንኳን የሩሲያን ወታደራዊ ግስጋሴን መግታት አልቻለም" ብላለች።
ጥቃቱ በየትኛው የሉሃንስክ ክፍል እንደተፈጸመ ሩሲያ አልገለጸችም።
ዩክሬን "እየነደደች" ባለችበት ወቅት የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃልኪዳን ድርጅት (ኔቶ) አባል ሀገራት የጦር መሳሪያዎችን ምርት እያሳደጉ ነው ተብሏል።
የኔቶ ዋና አዛዥ የንስ ስቶልተንበርግ በብራስልስ ለሁለት ቀናት ከተካሄደው የህብረቱ መከላከያ ሚንስትሮች ስብሰባ በኋላ “ሁነቶች እየተካሄዱ ነው፤ ነገር ግን... የበለጠ መጠናከር አለብን። ምክንያቱም ለዩክሬን ጥይት ለማቅረብ ትልቅ ፍላጎት አለ” ሲሉ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
ዩክሬን በቢሊዮን ዶላር የሚቆጠር ወታደራዊ እርዳታ ያገኘች ሲሆን፤ ጦርነቱ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ አሜሪካ ከ27 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር በላይ ድጋፍ እንዳደረግችላት ተገልጿል።