የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮልድሚር ዜለንስኪም በታህሳስ ወር መጨረሻ በአሜሪካ ሚስጢራዊ ጉብኝት ማድረጋቸው ይታወሳል
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በዩክሬን ያልተጠበቀ ጉብኝት ለማድረግ ኬቭ መግባታቸው ተነግሯል።
የዩክሬንና ሩሲያ ጦርነት አንደኛ አመቱን ሊይዝ አራት ቀናት ሲቀሩት ነው ፕሬዝዳንት ባይደን ኬቭ የገቡት።
ፕሬዝዳንቱ በድንገተኛው ጉብኝታቸው ኬቭ ሲደርሱ በዩክሬኑ አቻቸው ቮልድሚር ዜለንስኪ አቀባበል ተደርጎላቸዋል።
ባለፉት 12 ወራት ለዩክሬን ከ27 ቢሊየን ዶላር በላይ ድጋፍ ያደረገችው አሜሪካ፥ ለኬቭ ያላትን አጋርነት በፕሬዝዳንቱ ጉብኝት ይበልጥ ማሳየት ችላለች።
ኬቭ ከምዕራባውያን አጋሮቿ የተገባላት የጦር መሳሪያ ድጋፍም በፍጥነት እንዲቀርብ ባይደን እና ዜለንስኪ የሚያደርጉት ምክክር ትልቅ አበርክቶ እንደሚኖረው ይጠበቃል።
ዩክሬን፥ አሜሪካን ጨምሮ ከአውሮፓ አጋሮቿ ከ140 በላይ መድፎች በወራት ውስጥ ትረከባለች ተብሏል።
“ኤም1 አብራምስ” የተሰኘውን ታንኳን ወደ ኬቭ እልካለሁ ያለችው ዋሽንግተን፥ ጀርመንን ጨምሮ በርካታ ሀገራት የውጊያ ታንኮችን እና የጦር መሳሪያዎችን እንዲሰጡ ጫና ስታደርግ መቆየቷ የሚታወስ ነው።
ዩክሬንም ቃል የተገቡላት ታንኮች በፍጥነት እንዲቀርቡላትና የጦር ጄቶች ድጋፍም እንዲደረግላት መወትወቷን ቀጥላለች።
ፕሬዝዳንት ባይደን በኬቭ ቆይታቸውም ከአራት ቀናት በኋላ አንደኛ አመቱን የሚይዘው ጦርነት በኬቭ የበላይነት እንዲቋጭ ስለሚደረገው ድጋፍ ከዜለንስኪ ጋር ይመክራሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የባይደንን የዩክሬን ጉብኝት የተመለከቱ መረጃዎችን በሚስጢር ይዞ የቆየው ዋይትሃውስ፥ ስለጉብኝቱ ዝርዝር መረጃን ባያወጣም ለዩክሬን ስለሚደረገው ድጋፍና በሞስኮ ላይ ስለሚጣሉ ማዕቀቦች ምክክር እንደሚደረግ አስታውቋል።
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮልድሚር ዜለንስኪ በታህሳስ ወር መጨረሻ በአሜሪካ አስቀድሞ ያልተነገረለት ሚስጢራዊ ጉዞ አድርገው ከፕሬዝዳንት ባይደን ጋር መምከራቸው ይታወሳል።
ሩሲያ በዩክሬን ላይ ልዩ ያለችውን ወታደራዊ ዘመቻ ከከፈተች በኋላ አሜሪካን ጨምሮ ምእራባውያን ማዕቀብ እየደራረቡባት ነው።
ሞስኮ የዜለንስኪ የዋሽንግተን ጉዞ እንደተሰማ የብሄራዊ ደህንነት ምክር ቤት ምክትል ሊቀመንበሯን ዲሚትሪ ሜድቬዴቭ ወደ ቤጂንግ መላኳ አይዘነጋም።
ሃያላኑ በሁለት ጎራ የተሰለፉባት ዩክሬን የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃልኪዳን ድርጅት (ኔቶ) አባልነት ጉዳይ ይዞባት የመጣው ጦርነት አንድ አመት ሊደፍን ነው።