ሰሜን ኮሪያ ዩክሬን ኒውክሌር የመታጠቅ ዓላማ አላት አለች
የኪየቭ እንቅስቃሴ ሞስኮ ታክቲካል የኒውክሌር ጦር መሳሪያ በቤላሩስ ለማስፈር ማቀዷን ተከትሎ ነው
ፒዮንግያንግ በምዕራቡ ዓለም ለገጠማት መገለል ከክሬምሊን ጋር የጠበቀ ግንኙነት እየፈጠረች ነው ተብሏል
ሰሜን ኮሪያ ዩክሬን ኒውክሌር የመታጠቅ ዓላማ እንዳላት ገለጸች፡፡
የሰሜን ኮሪያ መሪ ኪም ጆንግ ኡን እህትና ጉምቱ ባለስልጣን ኪም ዮ ጆንግ ዩክሬን የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ለመታጠቅ ጥሪ አድርጋለች በማለት ክስ ሰንዝረዋል።
ኪም በፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ ቢሮ በኩል ጥሪ መቅረቡንና እንቅስቃሴው የፖለቲካ ሴራ ሊሆን ይችላል ብለዋል። ሆኖም ለጉዳዩ ምንም አይነት ማስረጃ አላቀረቡም ሲል ሮይተርስ ዘግቧል።
ሰሜን ኮሪያ በዉሃ ውስጥ ኑክሌር መሸከም የሚችል ድሮን ሙከራ አደረገች
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ባለፈው ሳምንት ታክቲካል የኒውክሌር ጦር መሳሪያን በቤላሩስ ለማስፈር እቅዳቸውን አስታውቀዋል።
ይህን ተከትሎ በዩክሬን ፕሬዝዳንታዊ ጽህፈት ቤት ድረ-ገጽ ዩክሬን የኒውክሌር ጦር መሳሪያ እንድትታጠቅ የሚጠይቅ ፊርማ እየዞረ ነው ተብሏል።
የኪየቭ ባለስልጣናት ስለ ፊርማው እስካሁን በይፋ ያሉት ነገር የለም።
ሰሜን ኮሪያ በምዕራቡ ዓለም የጋራ መገለል ከገጠማት ክሬምሊን ጋር የጠበቀ ግንኙነት እየፈጠረች ነው ተብሏል።
ፒዮንግያንግ ሩሲያ ባለፈው ዓመት ዩክሬንን ከወረረች በኋላ የሞስኮን አቋም ደግፋለች። ሆኖም ለሞስኮ የጦር መሳሪያ ማቅረብን በሚመለከት ክሱን ክዳለች።