ሰሜን ኮሪያ ጦሯ በየትኛውም ጊዜ የኒዩክሌር ጥቃት ለመፈጸም ዝግጁ እንዲሆን አሳሰበች
የሀገሪቱ መሪ ኪም ጆንግ ኡን በሳምንቱ መጨረሻ ሀገራቸው ባደረገችው ወታደራዊ ልምምድ የልባቸው መድረሱን ተናግረዋል
ፒዮንግያንግ ፥ አሜሪካ እና ደቡብ ኮሪያ የሚያደርጉትን ወታደራዊ ልምምድ ካላቋረጡ መዘዙ የከፋ ይሆናል እያለች ነው
የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን ለአሜሪካ እና ወዳጆቿ ጠንከር ያለ መልዕክት ከፒዮንግያንግ ማስወንጨፋቸው ተገልጿል።
አሜሪካ እና ደቡብ ኮሪያ ባለፈው ሳምንት የጀመሩትን ወታደራዊ ልምምድ በተደጋጋሚ የተቃወሙት ኪም ጆንግ ኡን፥ ባለፉት ሁለት ቀናት ጦራቸው ልዩ ወታደራዊ ልምምድ ሲያደርግ በአካል ተገኝተው መመልከታቸውን የሀገሪቱ ብሄራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ ዘግቧል።
ወታደራዊ ልምምዱ አህጉር አቋራጭ የኒዩክሌር አረር ተሸካሚ የባለስቲክ ሚሳኤል ሙከራን ጨምሮ ሊቃጡ የሚችሉ የኒዩክሌር ጥቃቶችን መመከት የሚያስችል መሆኑንም ነው ዘገባው ያመላከተው።
ኪም በዚሁ ወቅት ጦራቸው በተፈለገው ጊዜ የኒዩክሌር ጥቃት ለማድረስ ዝግጁ እንዲሆን ማሳሰባቸውም ተጠቅሷል።
- ሰሜን ኮሪያ ወደ 800ሺህ የሚጠጉ ዜጎቿ አሜሪካን ለመዋጋት መመዝገባቸውን አስታወቀች
- ሰሜን ኮሪያ አሜሪካና ደቡብ ኮሪያን ለማስጠንቀቅ የተኮሰችው ህዋሰኦንግ-17 ሚሳዔል እውነታዎች
በሳምንቱ መጨረሻ በተካሄደው ወታደራዊ ልምምድና ትርኢትም መሪው “የልባቸው መድረሱን” መናገራቸውን ዘገባው አክሏል።
አሜሪካ እና ደቡብ ኮሪያ ለ11 ቀናት የሚዘልቅ ወታደራዊ ልምምድ ማድረግ ከጀመሩ ወዲህ ፒዮንግያንግ አራት ጊዜ ወታደራዊ ትርኢት እና ልምምዶችን አድርጋለች።
አሜሪካን ሊያጠቃ የሚችል አህጉር አቋራጭ ባለስቲክ ሚሳኤልን ጨምሮ አጭር ርቀት ተምዘግዛጊ ሚሳኤሎችን ወደ ጃፓን እና ደቡብ ኮሪያ የባህር ክልሎች ማስወንጨፏም ይታወሳል።
የሚሳኤል ሙከራዎቹ ከመንግስታቱ ድርጅት ማዕቀቦች ያፈነገጡ ናቸው ያሉት ዋሽንግተን እና ሴኡል በፒዮንግያንግ ላይ ሊወሰድ ስለሚችል አዲስ እርምጃ እየመከሩ ነው ተብሏል።
ሰሜን ኮሪያ ግን ተቃውሞዋን በሚሳኤል ማስወንጨፍ መግለጧን ቀጥላለች።
ባለፉት ሁለት ቀናት ባካሄደችው ወታደራዊ ልምምድም የኒዩክሌር አረር የሚሸከሙ ባለስቲክ ሚሳኤሎችን እንዴት ማስወንጨፍ እንደሚቻል መለማመዷ ተገልጿል።
ፒዮንግያንግ ግን “የኒዩክሌር አረር የተሸከሙ በሚመስሉ ነገሮች” የተካሄደ እንጂ የምር አልነበረም ብላለች።