የሩሲያ ዋግነር ቡድን ከጄነራል ዳጋሎ ጎን በመሆን እየተዋጋ ነው- የሱዳን ጦር
በሱዳን ጦርና በፈጥኖ ደራሽ ኃይል መካከል የተቀሰቀሰው ጦርነት እንደቀጠለ ነው
ሄሜቲ በሀገር ክህደት እንደሚከሰሱና ወታደራ ማእረጋቸው እንደሚነጠቅም የሱዳን ጦር አስታውቋል
የሱዳን ጦር የሩሲያ ዋግነር ቅጥረኛ ተዋጊ ቡድን ከጄነራል ዳጋሎ ጎን በመሆን እየተዋጋ ነው ሲል ከሰሰ።
የሱዳን ጦር አመራር የሆኑት ሌተናል ጄነራል ያሲር አልአታ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በሰጡት አስተያየት፤ የሱዳን ጦር በሀገሪቱ ሰላም እና መረጋጋትን ለማስፈን እየሰራ እንደሆነ አስታውቀዋል።
በአሁኑ ወቅትም በጄነራል አብዱል ፈታህ አልቡርሃን የሚመራው የሱዳን ጦር ሁሉንም የሱዳን ክልሎች መቆጣጠሩን ነው ያስታወቁት።
ከተለያዩ ኪስ ቦታዎች ውጪ ጄነራል መሃመድ ሀምዳን ዳጋሎ የሚመራው ፈጥኖ ደራሽ ኃይል ተሸንፏል ያት ወታደራዊ አመራሩ፤ በተለይም የሁሉም ውጊያዎች እናት በተባለው ዋናው ማዘዣ ውጊያ ላይ መሸነፋቸውን አስታውቀዋል።
- የሩሲያው ዋግነር ቅጥረኛ ተዋጊ ቡድን እንደሚባለው ሱዳን ውስጥ አለ? ምንስ እያደረገ ነው?
- የሱዳን ጦር፣ የሄሜቲ ጦር ተጨማሪ ኃይል ከዳርፉር ወደ ካርቱም እያንቀሳቀሰ ነው ሲል ከሰሰ
ሌተናል ጄነራል ያሲር አልአታ አክለውም የፈጣኖ ደራሽ ኃይሉ ጄነራል መሃመድ ሀምዳን ዳጋሎ በቅጽል ስማቸው ሀሜቲ በሱዳን ግጭት እንዲነሳ አድርገዋል፤ የሱዳን ጦርንም ክደዋል ሲሉ ከሰዋል።
ሀሜቲ በከፍተኛ የሀገር ክህደት ወንጀል ክስ ይጠብቃቸዋል ያሉት ሌተናል ጄነራል ያሲር አልአታ፤ ሀሜቲ የጄነራልነት ማዕረጋቸው እንደሚነጠቅም ነው ያስታወቁት።
ሌተናል ጄነራል ያሲር አልአታ አክለውም የሩሲያ ዋግነር ቅጥረኛ ተዋጊ ቡድን ከጄነራል ዳጋሎ ኃሎች ጎን ተሰልፎ እየተወዋጋ ነው፤ አንድ የቡድኑ አባልም ተገድሏል ብለዋል።
የሱዳን ጦር ከዚህ ቀደምም ጦርነቱ መቀስቀሱን ተከትሎ “የሩሲያው ዋግነር ቅጥረኛ ተዋጊ ቡድን ራፒድ ሰፖርት ፎርስ (አር.ኤስ.ኤፍ) ተብሎ በሚጠራው ፈጥኖ ደራሽ ኃይል ዋና አዛዥ ጄነራል ሀምዳን ዳጋሎ (ሀሜቲ) ከለላ እየሰጠ ነው” ማለቱ ይታወሳል።
ሩሲያው ዋግነር ቅጥረኛ ተዋጊ ቡድን በበኩሉ በአሁን በሱዳን እየተካሄደ ባለው ጦርነት ውስጥ ምንም አይነት ተሳትፎ የለኝም ሲል የሚቀርብበትን ክስ ውድቅ አድርጎት ነበረ።
ከፕሬዝዳንት ፑቲን ጋር ቅርበት እንዳላቸው የሚነገርላቸው የዋግነር ቡድን መስራች የቭጌኒ ፕሪገዞሂን፤ “በአሁኑ ሰዓት አንድም የዋግነር ቡድን ተዋጊ በሱዳን ውስጥ የለም” ማለታቸውም አይዘነጋም።
የቭጌኒ አክለውም የቡድናቸው ተዋጊዎች በሱዳን ውስጥ ከሁለት ዓመታት ወዲህ ምንም አይነት እንቅስቃሴ አድርገው እንደማያውቁ አስታውቀዋል።