የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ጦርነቱ ወደጎረቤት ሀገራት ሊስፋፋ ይቻላል ሲሉ ሰግተዋል
ጦርነት ላይ የሚገኙት ሩሲያ እና ዩክሬን ጀምረውት የነበረውን ንግግር ሊቀጥሉ መሆኑ ተገለጸ።
በቤላሩስ እና በቱርክ የሰላም ንግግር ጀምረው የነበሩት ሀገራቱ ዛሬም ለመገናኘትና ንግግር ለማድረግ እንዳቀዱ ተገልጿል፡፡
ሩሲያ ትናንትና በፖላንድ አቅራቢያ ጥቃት ማድረሷን ተከትሎ ጦርነቱ ከሁለቱ ሀገራት አልፎ ወደ ሩሲያ እና ኔቶ እንዲሁም ወደ ሙሉ አውሮፓና ሩሲያ ሊስፋፋ ይችላል የሚል ስጋት ሲነሳ ነበር፡፡
የሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ ከዩክሬኑ አቻቸው ዲሚትሮ ኩሌባ ጋር በቱርክ በአካል መገናኘታቸው የተገለጸ ቢሆንም ንግግራቸው ግን ውጤት አላመጣም ተብሏል፡፡
ዛሬ ኪቭ እና ሞስኮ በተወካዮቻቸው በኩል ንግግር ያደርጋሉ ይባል እንጅ የትና በየትኞቹ ተወካዮቻቸው በኩል እንደሚገናኙ ግን በዝርዝር አልተገለጸም፡፡
አሜሪካንና ኔቶን በተደጋጋሚ እየተማጸኑ ያሉት የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ አሁን በሁለቱ ሀገራት መካከል የተጀመረው ጦርነት ወደ ጎረቤት ሀገራት ሊስፋፋ እንደሚችል አስጠንቅቀዋል፡፡
በዚህም መሰረት የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) ወደ ዩክሬን አውሮፕላን እንዳይበር ማድረግ እንዳለበት ገልጸዋል፡፡
ኔቶ እና አሜሪካ ቀደም ሲል በዩክሬን አውሮፕላን እንዳይበር ማድረግ ጦርነቱን ሊያስፋፋው እንደሚችል ከገለጹ በኋላ ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ ኔቶች “ደካማና የማይጠቅም” በሚል መዝለፋቸው ይታወሳል፡፡
ይህንን ዘለፋ ተከትሎ የኔቶ ዋና ጸሐፊ ጀንስ ስቶልተንበርግ የሰጡት ስለመኖሩ አልተገለጸም፡፡ ባሳለፍነው ሳምንት ሩሲያ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ጥበቃ ስብሰባ እንዲያደርግ መጠየቋን አስታውቃ ነበር፡፡
ሞስኮ ስብሰባው እንዲጠራ የፈለገችው በአሜሪካ እንደሚደገፍ በገመተችውና በዩክሬን አለ በተባለው የስ ህይወታዊ ጦር መሳሪያ (ባየሎጂካል ዊፐን) ጉዳይ መሆኑ ተገልጿል፡፡