ሩሲያ እና ዩክሬን ተኩስ ለማቆም ሳይስማሙ ቀሩ
በውይይቱ ሩሲያ ዩክሬን ኔቶን ላለመቀላቀሏ ዋስትና የሚሰጥ ህገ መንግስታዊ ማሻሻያ እንድታደርግ ጠይቃለች
በሃገራቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በቱርኳ አንታልያ ከተማ የተካሄደው ውይይት ያለ ስምምነት ተጠናቋል
ሩሲያ እና ዩክሬን ተክስ ለማቆም ሳይስማሙ ቀሩ፡፡
የሃገራቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በሜዲትራንያን ባህር ዳርቻ በምትገኘው የቱርክ የሪዞርት ከተማ አንታልያ ተገናኝተው ተወያይተዋል፡፡
ሆኖም በሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ እና በዩክሬኑ አቻቸው ዲሚትሮ ኩሌባ መካከል የተካሄደው ውይይት ያለ ስምምነት መጠናቀቁ ነው የተገለጸው፡፡
የዩክሬኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲሚትሮ ኩሌባ ከውይይቱ በኋላ በሰጡት ጋዜጣው መግለጫ “በዩክሬን-ሩሲያ መካካል የተኩስ አቁም ሂደትን በተመለከተ የተደረሰ ስምምነት የለም” ብለዋል፡፡
በውይይቱ ሩሲያ ዩክሬን ህገ መንግስታዊ ማሻሻያ አድርጋ የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅትን (ኔቶ) እንደማትቀላቀል እንድትገልጽ እና ክሬሚያ ሉዓላዊ የሩሲያ መሬት መሆኗን በይፋ እንድታውጅ ጠይቃለች፡፡
ዩክሬን በበኩሏ የሩሲያ ጦር ክሬሚያ እና ዶንባስ ግዛትን ጨምሩ ከሌሎች በወረራ ከያዛቸው ሉዓላዊ መሬቶቿ እንዲወጣ ጠይቃለች፡፡
ሆኖም ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቹ በቀረቡት ቅድመ ሁኔታዎች ሳይስማሙ ውይይቱን አጠናቀዋል፡፡
ሴርጌ ላቭሮቭ አደገኛ ጦር መሳሪያዎች ለዩክሬን እየቀረበ ነው ብለዋል፡፡ ዛሪ ማሪውፑል ከተማ በሚገኝ ሆስፒታል ላይ ስለተፈጸመው ጥቃት የተጠየቁት ሚኒስትሩ ሆስፒታሉ የዩክሬናውያን አክራሪዎች ማዘዣ ጣቢያ ሆኖ ሲያገለግል እንደነበር ገልጸዋል፡፡
ዲሜትሪ ኩሌባ በበኩላቸው በውይይቱ ተኩስ ለማቆም ሳይስማሙ መቅረታቸውን በማስታወቅ “ዩክሬን መቼም፣ አሁንም ወደፊትም በፍጹም እጅ አትሰጥም” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ውይይቱ ሶስት ሳምንታትን ገደማ ላስቆጠረው ጦርነት መቋጫ ለማበጀት የሚያስችሉ የመፍትሄ መንገዶችን ለማፈላለግ ያስችላል በሚል ተስፋ ተጥሎበት ነበር፡፡
በጦርነቱ 3 ሚሊዮን ገደማ ዜጎች መፈናቀላቸውን ተመድ አስታውቋል፡፡ ሩሲያ አንዲትን ሉዓላዊት ሃገር በመውረር የጦር ወንጀል እየፈጸመች መሆኑን ደጋግማ የገለጸችው ዩክሬን ኔቶ እና ምዕራባዊ አጋሮቿ የምትፈልገውን ያህል እንዳልደገፏት በመግለጽ በአደባባይ ስትወቅስ ተደምጣለች፡፡
አጋሮቿ በኪቭ የቀረበውን የበረራ እገዳ ጥያቄ አለመቀበላቸውም ዩክሬንን ደስ ሳያሰኝ ቀርቷል፡፡ በኔቶ ድክመት ሰዎች ህይወታቸውን እያጡ ነው ሲሉም ነው ፕሬዝዳንት ዜለንስኪ የወቀሱት፡፡
ቭላድሚር ፑቲን በበኩላቸው “በዩክሬን የተጀመረው ወታደራዊ ተልዕኮ” ሀገራቸው ባቀደችው መልኩ እየሄደ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የሩሲያ ጦር እስካሁን ባካሄደው “ዘመቻ” በደቡብ ዩክሬን የምትገኝው ኬርሶን ከተማ ጨምሮ ሌሎች ቦታዎችንና ከተሞችን መቆጣጠር ችሏል፡፡