ዩክሬን የሩሲያን አንድ ብርጌድ ከባክሙት ማስወጣቷን ገለጸች
የሩሲያ ቅጥረኛ ተዋጊ ቡድን ዋግነርም የሩሲያ 72ኛ ብርጌድ ከደቡብ ምዕራባዊ ባክሙት ማፈግፈጉን ነው ያስታወቀው
ክሬምሊን የኬቭንም ሆነ የዋግነር ቡድን አዛዡን መረጃ አላስተባበለም
ዩክሬን በሩሲያ ሃይሎች ተይዛ በምትገኘው ባክሙት ከተማ መጠነ ሰፊ ጥቃት እየወሰደች መሆኑን አስታውቃለች።
በዚህም በደቡብ ምዕራባዊ የከተማዋ ክፍል የነበረው የሩሲያ 72ኛ ብርጌድ እስከ 2 ኪሎሜትሮች ድረስ አፈግፍጎ ለመውጣት መገደዱን ነው የዩክሬን ምድር ጦር አዛዡ ጀነራል ኦሌክሳንደር ሲርስኪ የተናገሩት።
የሩሲያው ቅጥረኛ ተዋጊ ቡድን (ዋግነር) አዛዥ ይቪግኒ ፕሪጎዚንም ተዋጊዎቹ በትጥቅ አቅርቦት ችግር ከባክሙት ማፈግፈጋቸውን በትናንትናው እለት መግለጹ ይታወሳል።
ከ500 በላይ ወታደሮችም በዩክሬን መልሶ ማጥቃት ስለመገደላቸው ገልጿል።
ሬውተርስ በኬቭም ሆነ በዋግነር ቡድን መሪው የተሰጡ መረጃዎችን ማረጋገጥ አልቻልኩም ብሏል።
የሩሲያው ታስ የዜና ወኪል በበኩሉ፥ የባክሙት ዘመቻ እጅግ ፈታኝ መሆኑን የክሬምሊን ቃልአቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ መናገራቸውን ዘግቧል።
ፔስኮቭ “ባክሙት በሩሲያ ሃይሎች ሙሉ በሙሉ መያዟ አይቀርም” የሚል ንግግር ማድረጋቸውም የሩሲያ ጦር ማፈግፈጉን እንደሚያመላክት ተጠቅሷል።
ይሁን እንጂ የሩሲያ 72ኛ ብርጌድ ከባክሙት ስለማፈግፈጉ በቀጥታ ምላሽ ለመስጠት አልፈለጉም ነው የተባለው።
ሩሲያ በምስራቃዊ ዩክሬን መሰረተልማቶችን የሚያፈራርስ “ጦርነት ባለማወጇ” ሂደቱ አዝጋሚ ሆኗል የሚሉት የክሬምሊን ቃልአቀባይ፥ የዩክሬንን ወታደራዊ ኢላማዎች መደብደባችን እንቀጥላለን ሲሉ ተደምጠዋል።
በሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር እና በዋግነር ቡድን መካከል የሚታየው አለመግባባት በባክሙት በብዙ መስዋዕትነት የተገኘውን ድል ወደኋላ ሊመልሰው እንደሚችል የሞስኮ ተንታኞች ያነሳሉ።