ሩሲያ ከ78 አመት በፊት በናዚዎች ላይ የተቀዳጀችውን ድል እያከበረች ነው
ሩሲያ ወደ ዩክሬን መዲና ኬቭ 15 ክሩዝ ሚሳኤሎችን ማስወንጨፏ ተነግሯል።
ይሁን እኝጂ ሁሉም ሚሳኤሎች ኢላማቸውን ሳይመቱ ተመተው መውደቃቸውን የዩክሬን አየር ሃይል ይፋ አድርጓል።
ዛሬ ማለዳ ወደ ኬቭ የተተኮሱት ክሩዝ ሚሳኤሎች ተመተው ሲወድቁ በሰው ህይወት ላይ ጉዳት አለማድረሳቸውን የከተማዋ ወታደራዊ አዛዥ ሰርሂ ፖፕኮ በቴሌግራም ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።
የዛሬው ጥቃት የግንቦት ወር ከገባ ወዲህ አምስተኛው የሞስኮ መጠነሰፊ የጥቃት ሙከራ ነው ተብሏል።
ዩክሬን ከሞስኮ የሚቃጡ ጥቃቶች መጨመራቸውን ተከትሎ የአየር መቃወሚያ ስርአቷ በተጠንቀቅ እንዲጠባበቅ ካዘዘች ቀናት ተቆጥረዋል።
በዛሬው እለትም 15 የሩሲያ ክሩዝ ሚሳኤሎችን ስለመጣሏ የወዳደቁ የሚሳኤሎቹን ክፍሎች ከሚያሳዩ ምስሎች ጋር ብታወጣም ሞስኮ ምንም ምላሽ አልሰጠችም።
ሩሲያ በዛሬው እለት በ1945 የጀርመን ናዚዎችን ያሸነፈችበትን 78ኛ አመት የድል በዓል እያከበረች ነው።
በአደባባይ ወታደራዊ አቅሟን በምታሳይበት እለት በዩክሬን የተለያዩ ከተሞች የአየር ጥቃቷን ቀጥላለች ብሏል ሬውተርስ በዘገባው።
የድል በዓሉን እንደ ሩሲያ ሁሉ በዛሬው እለት ስታከብር የቆየችው ዩክሬን፥ የአሁኗን ሩሲያ ከናዚ ጀርመን ጋር በማመሳሰል በዓሉን እንደ አውሮፓ ሀገራት ግንቦት 8 አክብራ ለመዋል ረቂቅ ህግ አዘጋጅታለች።
ፕሬዝዳንት ቮልድሚር ዜለንስኪም “ሩሲያ በዩክሬን እንደ ናዚዎች መሸነፏ አይቀርም” የሚል መግለጫን ትናንት ሰጥተዋል።
የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ማሪያ ዛካሮቫ በስጡት ምላሽም፥ ፕሬዝዳንቱ ዩክሬናውያን በሁለተኛው የአለም ጦርነት የከፈሉትን መስዋዕትነት የከዱ “የ21ኛው ክፍለዘመን ይሁዳ” ናቸው ብለዋል።
ለዩክሬን ፓርላማ የቀረበውን ረቂቅ ህግ ያደነቁት የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽኝ ሊቀመንበር ኡርሱላ ቮን ደር ላይን በዛሬው እለት ኬቭ የገቡ ሲሆን፥ በጉዳዩ ዙሪያ ከዜለንስኪ ጋር ይወያያሉ ተብሏል።