ዩክሬን ከቤላሩስ ጥቃት ሊሰነዘርባት እንደሚችል ያላትን ስጋት ገለጸች
የዩክሬን ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም “የሩሲያ እና የቤላሩስ አመራሮች ጨካኝ ንግግሮች እየተጠናከሩ ነው” ብለዋል
የቤላሩስና የሩሲያ የጋራ ወታደራዊ ኃይል ማሰማራት በዩክሬን ያለው ሁኔታ ይበልጥ እንዳያባብሰው ተሰግቷል
ዩክሬን ከቤላሩስ ጥቃት ሊሰነዘርባት እንደሚችል ያላትን ስጋት ገለጸች፡፡
ኪቭ ይህን ያለችው የወቅቱ ቤላሩስና ሩሲያ መግለጫዎች እንዲሁም የቤላሩስ ድንበሮችን ለመከላከል ኃላፊነት የተሰጠው አዲስ ኃይል ከተፈጠረ በኋላ ነው፡፡
የዩክሬን ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ኦሌክሲ ግሮሞቭ በሰጡት መግለጫ “የሩሲያ እና የቤላሩስ ወታደራዊ-ፖለቲካዊ አመራር ጨካኝ ንግግሮች እየተጠናከሩ ነው” ብለዋል ።
"በሰሜናዊው ግንባር በሩሲያ የጦር ኃይሎች የሚካሄደው ጥቃት እንደገና የመቀጠሉ ጉዳይ ስጋት እየፈጠረ ነው" ሲሉም አክለዋል ግሮሞቭ፡፡
ቀደም ሲል ሐሙስ እለት የቤላሩስ የደኅንነት አገልግሎት በመንግስት በሚተዳደረው ቤልታ ኤጀንሲ በሰጠው መግለጫ “በየቀኑ ማለት ይቻላል ከዩክሬን ግዛት እየጨመረ የሚሄደውን የስለላ እንቅስቃሴዎች እና የቤላሩስ አየር ክልልን ለመጣስ ሙከራዎች እናያለን” የሚል መረጃ አውጥቶ እንደነበር ይታወሳል፡፡
ከቤላሩስ ወታደሮች ጋር አዲስ የተቀናጀ ጦር ኃይል ይፈጥራሉ የተባሉት የመጀመሪያዎቹ የሩሲያ ወታደሮች ቤላሩስ መግባታቸውን የሚንስክ የመከላከያ ሚኒስቴር ከቀናት በፊት አስታውቆ ነበር፡፡
እስከ 9ሺህ የሚደርሱ የሩስያ ወታደሮች እና 170 ታንኮች ወደ ቤላሩስ እንደሚሰማሩም የሮይተርስ ዘገባ ያመለክታል፡፡
የፑቲን የቅርብ ወዳጅ የቤላሩስ ፕሬዝዳንት አሌክሳንደር ሉካሼንኮ የጋራ ወታደራዊ ኃይል ተልዕኮ "የድንበርን ለማጠናከር ብቻ ነው" ብለዋል፡፡
የአሁኑ የቤላሩስና የሩሲያ የጋራ ወታደራዊ ኃይል በዩክሬን ያለው ሁኔታ ይበልጥ እንዳያባብሰው ተሰግቷል ሲል ኤኤፍፒ ዘግቧል፡፡
የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ በቡድን-7 ጉባኤ ላይ ባሰሙት ንግግር “ሩሲያ ቤላሩስን በቀጥታ ወደዚህ ጦርነት ለመሳብ እየሞከረች ነው” ሲሉ ከሰዋል፡፡