ማዳጋስካር የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯን ሩሲያን ተቃውመው ድምጽ ሰጥተዋል በሚል ከስራ አገደች
የመንግስታቱ ድርጅት ከቀናት በፊት የሩሲያን ህዝበ ውሳኔ የሚቀወም ውሳኔ በአብላጫ ድምጽ መወሰኑ ይታወሳል
ሚኒስትሩ ከስራ የታገዱት በተመድ ጉባኤ ላይ ሩሲያን ተቃውመው ድምጽ ሰጥተዋል በሚል ነው
ማዳጋስካር የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯን ከሩሲያ ጋር በተያያዘ ከስራ አገደች።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅትአባል ሀገራት ባሳለፍነው ሳምንት ሩሲያ የዩክሬን ግዛት በሆኑ አራት ክልሎችን በህዝበ ውሳኔ ወደ ሯሷ መጠቅለሏን በሚመለከት ለውይይት ተቀምጠው ነበር።
ከ193 የተመድ አባል ሀገራትም 143ቱ የሩሲያን ህዝበ ውሳኔ በመቃወም በአብላጫ ድምጽ የወሰኑ ሲሆን አብዛኞቹ የአፍሪካ ሀገራት በጉዳዩ ላይ ድምጸ ተዓቅቦ አድርገዋል።
በዚህ የተመድ ውሳኔ ላይ 35 ሀገራት ደምጽ ተዓቅቦ ያደረጉ ሲሆን 18ቱ የአፍሪካ ሀገራትከ ሲሆኑ ኢትዮጵያም ከነዚህ ውስጥ አንዷነበረች።
ማዳጋስካር የሩሲያን ህዝበ ውሳኔ ተቃውመው በተመድ ጉባኤ ላይ ድምጽ ከሰጡ ሀገራት መካከል አንዷ ስትሆን በዚህ ድርጊት ላይ ዋነኛው ሰው ናቸው የተባሉት የሀገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከስራ መታገዳቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
በፕሬዝዳንት አንድሪ ራጆሊና የሚመራው የማዳጋስካር መንግስት ሪቻርድ ራንድሪያንድራቶ የተሰኙት ውጪ ጉዳይ ሚኒስትርን ከስራ አግደዋል ተብሏል።
በሩሲያ ዩክሬን ጦርነት ምክንያት ከዓለም ምግብ እና ነዳጅ ዋጋ መናር ባለፈ በርካታ ሀገራት የዲፕሎማሲ ውጥረት ውስጥ እንደገቡ ይጠቀሳል።
በተለይም የአፍሪካ ሀገራት ከምዕራባዊያን እና ሩሲያ ጋር የጠበቀ ግንኙነት ያላቸው ሲሆኑ አሜሪካንን ጨምሮ ሌሎች ምዕራባዊያን ደግሞ አፍሪካ ከሞስኮ ጋር ያላቸውን ግንኙነት እንዲያቋርጡ እና እንዲያላሉ በመወትወት ላይ ናቸው።
ባሳለፍነው ረቡዕ በተካሄደው የተመድ ጉባኤ ላይ 35 የዓለማችን ሀገራት ድምጸ ተዓቅቦ ሲያደርጉ ሩሲያ፣ ቤላሩስ፣ ሰሜን ኮሪያ፣ ሶሪያ እና ኒው ካራጉዋ ደግሞ የተመድን የውሳኔ ሀሳብ ተቃውመው ድምጽ ሰጥተዋል።