ዩክሬን ከ2ኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ በአውሮፓ ውስጥ ታይቶ የማያውቅ “ጭካኔ” እያጋጠማት ነው -የኔቶ ዋና አዛዥ
ዋና አዛዡ የኔቶ አባል ሀገራት ዩክሬንን በቀጣይነት ማገዝ እንዳለባቸውም አሳስበዋል
ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜለንስኪ በማድሪዱ የኔቶ ጉባኤ ላይ ንግግር ደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል
ዩክሬን ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ በአውሮፓ ውስጥ ታይቶ የማያውቅ 'ጭካኔ' እያጋጠማት ነው ሲሉ የኔቶ ዋና አዛዥ ጄንስ ስቶልተንበርግ ተናገሩ፡፡
ዋና አዛዡ በማድሪድ ወደ ሚደረገው የመሪዎች ጉባኤ የሚያመሩ የህብረቱ መሪዎች፤ ዩክሬን ከሩሲያ መጠነ ሰፊ ጥቃት እየተሰነዘረባት በመሆኑ፤ የኔቶ አባል ሀገራት ዩክሬንን መደገፋቸው ሊቀጥሉ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
ስቶልተንበርግ “ዩክሬን አሁን ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ በአውሮፓ ያላየነው ጭካኔ ስላጋጠማት የምናደገው ድጋፍ ለመቀጠል ዝግጁ መሆን አስፈላጊ ነው”ም ማለታቸውም ሮይተርስ ዘግቧል ።
የኔቶ አጋሮች የክሬምሊንን ሃይል ለማስቆም በሚደረገው ጥረት - ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የሚሄደውን ከባድ እና ረጅም ርቀት የሚምዘገዘጉ መሳሪያዎችን ጨምሮ በቢሊዮን ዶላሮች የሚገመቱ የጦር መሳሪያዎች ወደ ኪቭ ማስገባታቸው የሚታወቅ ነው።
ሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ)፡ በማድሪድ በሚያካሄደው የመሪዎች ጉባኤ ላይ ፤ ደህንነታቸው የተጠበቀ የመገናኛ መሳሪያዎች፣ ጸረ-ድሮን ሲስተሞች እና ዩክሬን በረጅም ጊዜ ውስጥ ወደ ዘመናዊ የምዕራባውያን የጦር መሳሪያዎች እንድትሸጋገር በሚያግዝ የጋራ ፓኬጅ ዙሪያ ለመስማማት ተዘጋጅቷል።
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜለንስኪ በትዊተር ገጻቸው እንዳሰፈሩት “የሩሲያ የሽብር ጥቃቶችን ለመከላከል፤ ጠንካራ የሚሳኤል መከላከያ ስርዓት ለዩክሬን እንሚያስፈልጋት” ከስቶልተንበርግ ጋር አውርተናል ብለዋል፡፡
ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜለንስኪ በማድሪዱ የኔቶ ጉባኤ ላይ ንግግር ደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ሩሲያ በዩክሬን ላይ እየተቀዳጀችው ያለው ወታደራዊ ድል ያሰጋው የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) የጦሩን ቁጥር ለማሳደግ እየሰራ መሆኑ የድርጅቱ ዋና ጸሃፊ ጄንስ ስቶልተንበርግ በትናንትናው እለት ማስታወቃቸው አይዘነጋም፡፡
ዋና ጸሃፊው በቀጣይ ቀናት በማድሪድ ከሚካሄደው ስብሰባ በፊት ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት “የኔቶን ኃይል እናጠናክረዋለን እንዲሁም የከፍተኛ ዝግጁነት ሀይላችንን ቁጥር ከ 300 ሺህ በላይ እናሳድጋለን" ብለዋል፡፡