ወታደሩ በንጹሃን ግድያ ነው አድሜ ይፍታህ የተባለው
ዩክሬን በ21 ዓመቱ ሩሲያዊ ወታደር ላይ እድሜ ይፍታህ ፈረደች፡፡
ቫዲም ሺሺማሪ እንደሚባል የተነገረለት ወታደሩ ጦርነቱ በተጀመረ በአራተኛው ቀን አንድን ያልታጠቀ የ62 ዓመት ጎልማሳ ተኩሶ ገድሏል ተብሏል፡፡
ሊጠቃ የሚችልበት አጋጣሚ በሌለበት ሁኔታ ኦሌክሳንድር ሼሊፖቭ የሚባለውን ጎልማሳ ጭንቅላቱን መቶ መግደሉን በማመኑ ነው ሺሺማሪ የተፈረደበት፡፡
ሺሺማሪ ዩክሬን ለፍርድ ያቀረበችው የመጀመሪያው የሩሲያ ጦር ምርኮኛ ነው፡፡ ውሳኔውን በተመለከተ በአንድ ወር ውስጥ አቤት ሊል እንደሚችልም ተገልጿል፡፡
የፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ቃል አቀባይ ዲሜትሪ ፔስኮቭ የዜጋቸው ሁኔታ እንደሚሳስባቸው ገልጸው ሊታገዝ የሚችልበትን መንገድ እንደሚፈለግ ተናግረዋል፡፡
"በአሁኑ ወቅት በኪቭ የሚንቀሳቀሱ ዓለም አቀፍ ተቋማት ባለመኖራቸው ተጨባጭ ፍላጎቶቹን ልናስፈጽም የምንችልበት ያን ያህል እድሉ የለንም፤ ሆኖም የምናማትራቸው ሌሎች አማራጮች የሉም ማለት አይደለም" ብለዋል ፔስኮቭ፡፡
ሆኖም አማራጮቹ ምን ዐይነት እንደሆኑ አልገለጹም፡፡
ሩሲያ የወታደሩን መከሰስ በመቃወም በንጹኃን ግድያ ወንጀል ፈጽሟል መባሉን አስተባብላ ነበር፡፡ ሆኖም ቫዲም ሺሺማሪ ግድያውን መፈጸሙን አምኖ በድርጊቱ መጸጸቱን በመግለጽ ይቅርታ ጠይቋል፡፡