ዩክሬን “ጦርነት ለማቆም በሚል ግዛቴን ለሩሲያ አሳልፌ አልሰጥም” አለች
የፖላንዱ ፕሬዝዳንት አንድረዘጅ ዱዳ በዩክሬን ፓርላማ ተገኝተው ንግግር ያሰሙ የመጀመርያው መሪ ሆነዋል
የፕሬዝዳንት ዘለንስኪ አማካሪ “ግዛት ማስረከብ ለከፋ ወረራና ደም አፋሳሽ ጦርነት የሚያጋልጥ ነው”ብለዋል
የዩክሬን መንግስት ጦርነት ለማቆም ግዛቱን ለሩሲያ አሳልፎ በመስጠት በሚደረግ የተኩስ ማቆም ድርድር እንደማይስማማ አስታወቀ።
ዩክሬን ይህን ጠንከር ያለ መግለጫ የሰጠችው የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ “ጦርነቱ የሚቆመው በዲፕሎማሲ ብቻ ነው” ማለታቸውን ተከትሎ ነው።
የፕሬዝዳንቱ አማካሪ ሚኻይሎ ፖለዶልያክ በሰጡት ማብራርያ “ግዛት ማስረከብ ለከፋ ወረራ እና ደም አፋሳሽ ጦርነት የሚያጋልጥ ነው” ብለዋል።
ሚኻይሎ ፖለዶልያክ፤ ይህን ያሉት የሩሲያ ኃይሎች በምስራቅ ዩክሬን የምትገኘውን ሰቨሮዶነስክን በመከለላከል ላይ ያሉትን የዩክሬን ኃይሎች በከበባ ውስጥ አስገብተው ለማጥቃት እያደረጉት ያለውን ከፍተኛ ጥረት ከግምት በማስገባት ነው።
በሌላ በኩል፤ የፖላንዱ ፕሬዝዳንት አንድረዘጅ ዱዳ በትናትናው እለት በዩክሬን ፓርላማ ተገኝተው ንግግር ያደረጉ ሲሆን፤ በዚህም በሀገሪቱ ፓርላማማ ንግግር ያደረጉ የመጀመርያው መሪ ሆነዋል።
ፕሬዝዳንት ዱዳ በፓርላማ ንግግራቸው “የዩክሬንን መጻኢ እጣፈንታ የሚወስኑት ዩክሬናውያን ብቻ ናቸው” ሲሉ ተድመጠዋል። በዚህም የፓርላማው አባላት ቆመው አጨንጭበውላቸል።
ዱዳ፤ ዩክሬን ወደ አውሮፓ ህብረት እንድትቀላቀል ሀገራቸው የሚቻላትን ሁሉ እንደምታደርግም ማናገራቸውም ሮይተርስ ዘግቧል።
ዱዳ ይህን ይበሉ እንጂ፤ የዩክሬን ወደ አውሮፓ ህብረት የመቀላቀል ጉዳይ አስርት ዓመታት ሊፈጅ እንደሚችል የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ማክሮን መናገራቸው የሚታወስ ነው።
ፕሬዝዳንቱ ከሳምንት በፊት በስትራስበርግ ለአውሮፓ ህብረት ፓርላማ ባሰሙት ንግግር እንዳሉት፤ አሁን ባለው የህብረቱ አሰራር የዩክሬን ጉዳይ ጊዜ እንዲፈጅ የሚያደርግ መሆኑ ተናግሯል።
ማክሮን በሰጡት አስተያየት "ወደ ህብረቱ የመቀላቀል ሂደቱና አሰራሩ ዓመታት ሊፈጅ እንደሚችል ሁላችን አናውቃለን" ብሏል።
መስፈርቱን ዝቅ ለማድግ ካልወሰንን እውነታው ይህ ነው ፤ ለአውሮፓ አንድነት ስንል ደግመን ማሰብ አለብን” ሲሉም አክሏል ማክሮን።
ማክሮን፤ የዩክሬን አባልነትን ለማቀላጠፍ በሚል የህብረቱ መስፈርቶችን ከመድፈቅ ይልቅ ከአውሮፓ ህብረት በላይ የሆነና ብሪታንያን ሊያካትት የሚችል “አቻ አውሮፓዊ የፖለቲካ ማህበረሰብ” ማቋቋም እንደ አማራጭ ማየቱ ተገቢ መሆኑም ምክረ-ሃሳብ አቅርበዋል።
"ይህ በጂኦግራፊ ከአውሮፓ ህብረት ውጭ ያሉትን ሀገራት ለመያዝ የምንችልበትና እሴቶቻችንን ለማካፈል የምንችልበት መንገድ ነው"ም ብለዋል ማክሮን።
ዩክሬን ወደ አውሮፓ ህብረት የመቀላቀል ጥያቄ ያቀረበችው፤ የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ ከአራት ቀናት በኋላ እንደነበር የሚታወስ ነው።