"ዲፕሎማሲ ብቻ ነው ጦርነቱን ሊቋጭ የሚችለው" - የዩክሬን ፕሬዝዳንት
ዜሌንስኪ ጦርነቱን በተመለከተ ቀደም ሲል የተጀመሩ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች በቆሙበት ሁኔታ ነው ይህን ያሉት
ጦርነቱ ደም አፋሳሽ ሊሆን ቢችልም የሚቋጨው በዲፕሎማሲያዊ መንገዶች ነው ሲሉም ተናግረዋል
የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ ሃገራቸው ከሩሲያ ጋር የያዘቸው ጦርነት ሊቋጭ የሚችለው በዲፕሎማሲ ብቻ መሆኑን ተናገሩ፡፡
ዜሌንስኪ ጦርነቱን በተመለከተ ቀደም ሲል የተጀመሩ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች በቆሙበት ሁኔታ ነው ይህን ያሉት፡፡
ጦርነቱ ደም አፋሳሽ ሊሆን ቢችልም የሚቋጨው በዲፕሎማሲያዊ መንገዶች ነው ሲሉም ለሃገራቸው የቴሌቪዥን ጣቢያ ተናግረዋል፡፡
መቼ፣ የት እና በእነ ማን በኩል ወይም በመሪዎች ደረጃ ሊሆን እንደሚችል በውል ባያውቁትም በዩክሬን እና በሩሲያ መካከል ውይይቶች እንደሚካሄዱ ግን ዜሌንስኪ በእርግጠኝነት ተናግረዋል፡፡
"በድርድር ብቻ የሚፈቱ ጉዳዮች አሉ፤ ሩሲያ አልፈቀደችም እንጂ ሁሉም ነገር ወደነበረበት እንዲመለስ እንፈልጋለን"ም ብለዋል፡፡
የድርድሩን ውጤት ምን ሊሆን እንደሚችል ለመገመት ባይቻልም ነገሮች ለዩክሬን ፍትሐዊ ሊሆኑ ይገባል ሲሉም ነው ዜሌንስኪ ያሳሰቡት፡፡
ዩክሬን ስለሚያስፈልጋት የደህንነት ዋስትና ሰነድም ተናግረዋል፡፡ ሰነዱ በወዳጆቿ እና በአጋሮቿ ሊፈረም እንደሚችልም ገልጸዋል፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን ከሩሲያ ጋር የሁለትዮሽ ውይይቶች ሊደረጉ እንደሚችልም አስቀምጠዋል፡፡
ሩሲያ በማሪዎፖል ከተማ ከሚገኘው የአዞቭስታል ብረት ፋብሪካ የማረከቻቸውን የዩክሬን ወታደሮች እንዳትገድል ጥብቅ ቅድመ ሁኔታዎች መቀመጣቸውንም ገልጸዋል ፕሬዝዳንቱ፡፡
ሞስኮው በማሪዎፖል መሽገው የነበሩ የመጨረሻዎቹ የዩክሬን ወታደሮች እጅ መስጠታቸውን አስታውቃለች፡፡
እስካሁን 1 ሺ 900 የዩክሬን ወታደሮች እጅ መስጠታቸውንም የሩሲያ ጦር አስታውቋል፡፡ ወታደሮቹ ላለፉት ሶስት ወራት በአዞቭስታል ብረት ፋብሪካ ውስጥ መሽገው የነበሩ ናቸው፡፡