ዩክሬን ለሁለተኛ ጊዜ የሩሲያ ስለላ አውሮፕላን መምታቷን ገለጸች
ኤ-50 የተሰኘው የሩሲያ ወታደራዊ አውሮፕላን ከዩክሬን ድንበር 200 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ተመቷል ተብሏል
የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ ዛሬ ሁለት ዓመት ሞልቶታል
ዩክሬን ለሁለተኛ ጊዜ የሩሲያ ስለላ አውሮፕላን መምታቷን ገለጸች፡፡
በዛሬው ዕለት ነበር ሩሲያ ለሁለት ሳምንት ልዩ ዘመቻ በሚል ጦሯን ወደ ዩክሬን የላከችው፡፡ በዚህ ጦርነት ምክንያት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ከቤት ንብረታቸው ሲፈናቀሉ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎችም ተገድለዋል፡፡
ሩሲያ አራት የዩክሬን ግዛቶችን ወደ ራሷ የጠቀለለች ቢሆንም ዩክሬን የሩሲያን ድንበር አልፋ የአየር ላይ ጥቃቶችን በማድረስ ላይ ትገኛለች፡፡
ሩሲያን ከድቶ ወደ ዩክሬን የኮበለለው አብራሪ ተገደለ
በትናንትናው ዕለትም ኤ-50 የተሰኘ የሩሲያ ስለላ አውሮፕላን በራሷ የሩሲያ ግዛት ውስጥ መትታ መጣሏን ዩክሬን አስታውቃለች፡፡
ቢቢሲ የዩክሬን ባለስልጣናትን ዋቢ አድርጎ እንደዘገበው ወታደራዊ የስለላ ስራዎችን ለማከናወን ጥሩ አውሮፕላን ነው የሚባለው ይህ ኤ-50 አውሮፕላን ከዩክሬን ድንበር 200 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ እንደተመታ ተገልጿል፡፡
ሩሲያ እስካሁን በዩክሬን ተመታ ስለተባለው የስለላ አውሮፕላን ጉዳይ መግለጫ ያላወጣች ሲሆን ሞስኮ በዩክሬን ላይ ከሰሞኑ የተቀዳጀችውን ድል ለማክበር በዝግጅት ላይ ነበረች ተብሏል፡፡
ዩክሬን በበኩሏ የሩሲያን አውሮፕላን ስትመታ እና በእሳት ሲያያዝ የሚያሳየውን ተንቀሳቃሽ ምስል እንኳን ደስ አለን ስትል ይፋ አድርጋለች፡፡
አውሮፕላኑ ተመቶ ወድቆበታል የተባለው የሩሲያዋ ክራስኖዳር ግዛት የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች ባወጡት መግለጫ የአውሮፕላን መከስከስ አደጋ እንዳጋጠመ ይፋ አድርጓል፡፡
ዩክሬን ከአንድ ወር በፊት ተመሳሳይ የስለላ አውሮፕላን መትታ መጣሏን የገለጸች ሲሆን ሩሲያ ይህንን አውሮፕላን ለመስራት በመቶዎች የሚቆጠር ዶላር ታወጣለች ተብሏል፡፡