ሩሲያ ባሳለፍነው ሳምንት የዩክሬኗ አዲቭካ ከተማን መቆጣጠሯ ይታወሳል
የሩሲያ ጦር በዩክሬን ዶኔስክ ክልል የምትገኘውን ፖቤዲያ የተባለችውን መንደር መቆጣጠሩን የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር አስታወቀ።
ፖቤዲያ በዩክሬኗ ማሪዪንካ ከተማ ደቡብ አቅጣጫ የምትገኝ ሲሆን፤ ለወራት ውጊያ ስደረግባት እንደነበረ ሮይተርስ ዘግቧል።
የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር ዶኔስክ ክልል የምትኘውን ፖቤዲያ በሩሲያ ጦር እጅ መውደቋን ተከትሎ ባወጣው መግለጫ፤ የተገኘው ድል የሩሲያ ጦር በዶኔስክ ክልል ሌሎች አካባዎች ላይ ድልን እንዲቀዳጅ የሚያጠናክር ነው ብሏል።
የዩክሬን ጦር በበኩሉ በአካባቢው ከሩሲያ እየተሰነዘሩ ያሉ በርካታ ጥቃቶችን እየመከተ እንደሆነ አስታውቋል።
የዩክሬን ጦር ዋና አዛዥ ትናንት በፌስቡክ ገጹ ባወጣው መረጃ የዩክሬን ጦር በፖቤዲያ እና ኖቮማይካቫ አካባቢዎች ላይ ከፍተኛ ውጊያ ማድረጉን እንደቀጠለ አስታውቋል።
“በአየር ኃይል የታገዘ የጠላት ኃይል የሰራዊታችንን መከላከያ 31 ጊዜ ለመስበር ሙከራ አድርጓል” ብሏል የዩክሬን ጦር በሪፖርቱ።
በዩክሬን ከፍተኛ ተነባቢ የሆነው የመከላከያ ብሎግ “ዲፕስቴት” በበኩሉ የሩሲያ ጦር ፖቤዲያን መቆጣጠሩን እና ሌሎች ሁለት መንደሮችን ለመቆጣጠር እየተጠጋ መሆኑን አስነብቧል።
የሩሲያ ጦር ባሳለፍነው ሳምንት የዩክሬኗ አዲቭካ ከተማን መቆጣጠሩ ይታወሳል።
ሩሲያ አዲቭካ ከተማን መቆጣጠሯ በፈረንጆቹ ግንቦት 2023 ባክሙትን ከተቆጣጠረች በኋላ ያስቆጠረችው ትልቁ ድል እንደሆነም ተነግሯል።
በሩሲያ ወደተያዘችው ዶኔስክ መግቢያ በር የሆነችው አቭዲቭካ ለወራት በተካሄደው ጦርነት ፈራርሳለች፤ ከ34 ሺህ በላይ ሰዎች መኖሪያ በነበረችው ከተማ አሁን 1 ሺህ ገደማ ሰዎች ይኖሩባታል ተብሏል።